You are here: HomeTheologyደ’ሞ የእግዚአብሔር አቻ ሆንን!?

ደ’ሞ የእግዚአብሔር አቻ ሆንን!?

Written by  Saturday, 30 July 2016 05:08

ኢትዮጵያዊቷ ቤተ ክርስቲያን የተዘፈቀችባቸው ድብልቅልቅ አስተምህሮዎች ዕለት ዕለት እየተበራከቱ፣ መልኳ ተዝጐርጕሮ አሳሳች ከሆነ ከራረመ። ለሕዝበ ክርስቲያኑ በአብዛኛው የሚቀርብለት፣ ራስን ያለ መጠን በማግነን መለኮት-አከል ለመሆን መንጠራራትን እና ምኞትን ያለ ቅጥ ማሳደድን የሚፈቅድ፣ ራስ መር ትምህርት ነው። ከዚህም በላይ የስሕተቶቹ ሁሉ መነሻና መውደቂያ የክርስቶስ ማንነት ነው፤ ለነገሩማ በታሪክ ውስጥ የተነሡ ዋና ዋና አሳቾች ዋናው ችግራቸው የክርስቶስ ማንነት ነው። በእኛም ዘመን የነጻነቱ ዘመን እንዲህ ዐይነቶቹ መርዛማ ትምህርቶች በዘመናዊው ቴክኖሎጂ ተጭነው፣ በጓዳችንና በአደባባያችን ያለ ከልካይ እንዲጋልቡ ፈቅዶ፣ የነጻነት መዘዝን አስከትሎብናል። ማንም ምንም ቢያስተምር መድረክ ያገኛል! አማኞችም ቢሆኑ በወንጌል ስም የሚቀርብላቸውን መርዛማ ሥራ ሥር ሁሉ ከመጉረስ ወደ ኋላ አለማለታቸው ክፉኛ ያስደነግጣል።

 

ይህንን ዐይነቱን ትምህርት በኤልሻዳይ እና በEBS ቴሌቭዥን ማሠራጫዎች እና በሌሎችም መስኮች ከሚነዙት “አስተማሪዎች” አንዱ ኀይሉ ዮሐንስ ነው። ከግለ ሰቡ አስተምህሮዎች መካከል “እኛ እና አብ አንድ ነን”፣ እንዲሁም እኛና እግዚአብሔር “አንዳችም ልዩነት የሌለን፣ ሙሉ በሙሉ አንድ ዐይነት ነን (We are exactly like God.)” የሚለው፣ እንዲሁም በክርስቶስ ማንነት ላይ ያለው መሳከር የዚህ ጽሑፍ ዋና አትኵሮት ይሆናል።[1]

 

ይህ ጽሑፍ በይፋ ከመለቀቁ ከአንድ ሳምንት በፊት በቀጥታ ለኀይሉ ዮሐንስ እንዲደርሰው በማድረግ ፊት ለፊት ለመገናኘት ቀጠሮ ተይዞ ነበር። እርሱም፣ በጽሑፉ ውስጥ “የእርሱ ናቸው” ተብለው የተጠቀሱት ሐሳቦች በትክክልም የእርሱ መሆናቸውን፣ ያልተናገራቸው ነገሮች አለመጠቀሳቸውን በማረጋገጥ፣ ትክክል ቢሆኑም ባይሆኑም ለትምህርቶቹ ኀላፊነት እንደሚወስድ ለዚህ ጸሓፊ በስልክ ነግሮታል። ፊት ለፊት የመገናኘቱን ቀጠሮ ግን ሰርዞ ሌሎች ቀጠሮዎችን ለማበጀት ቢሞከርም፣ ሳይሆንለት ወደ አሜሪካ ተመልሷል። የሆኖ ሆኖ፣ የክርስቶስን ወንጌል የማጣመምና የብዙዎችን ሕይወት የማናጋት ኀላፊነት እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም። ጕዳዩ ከዚያም ያልፍና እውነትን ለመቀበል ባለመፈለግ በእግዚአብሔር እውነት ላይ ከማመፅ ጋር ይያያዛል። አንድ አስተምህሮ ወይም ድርጊት ስሕተት መሆኑ እየታወቀ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” በማለት፣ በዚያው መንገድ መቀጠል ዐመፃ ነውና!

 

  1. እኛ እና እግዚአብሔር አንድ ነን

ኀይሉ ዮሐንስ በኤልሻዳይ ቴሌቭዥን ኔትወርክ በኩል፣ ከተሾመ ዳምጠው (መጋቢ) ጋር ያደረገውን ሙግት ተመልክቼዋለሁ። ሙግቱ በመጋቢ ተሾመ ጠያቂነት መካሄዱ፣ ለእውነት ቃል የሚቈረቈሩ ሰዎች መኖራቸውን የሚያሳይና ተስፋ የሚሰጥ ድርጊት ነው። የኤልሻዳይ ቴሌቭዥንም ለሙግቱ መድረክ በማመቻቸቱና ዝግጅቱንም በቀጥታ በማስተላለፉ ሊመሰገን ይገባል። ከዚህ በመቀጠል፣ የቴሌቭዥን ጣቢያው የኀይሉ ዮሐንስ ዝግጅቶች እንዳይተላለፉ ማገዱ ይበል የሚያሰኝ ውሳኔ ነው፤ ከተገቢው ጊዜ እጅግ የዘገየ ቢሆንም። ከአሁን በኋላም ጣቢያው ለእግዚአብሔር ቃልና ለጤናማው አስተምህሮ ያለውን ከበሬታ በዚህ መልክ እየቃኘ፣ ጕዞውን እንደሚቀጥል የዚህ ጸሓፊ እምነት ነው!  

 

ኀይሉ ዮሐንስ፣ “እኔና አብ አንድ ነን” ስለ ማለቱ በመጋቢ ተሾመ ጥያቄ ሲቀርብለት፣ “እኔና እግዚአብሔር አንድ ነን” እንጂ፣ “እኔና አብ አንድ ነን” በማለት እንዳልተናገረ ለማስተባበል ቢሞክርም፣ መጋቢው የቪዲዮ ማስረጃውን በማቅረቡ ኀይሉ ዮሐንስ እውነታውን ለመቀበል ተገድዷል። በቅርቡ በEBS ቴሌቭዥን በኩል ስለ ብልጽግና ባቀረበው ዝግጅትም፣ ይህንን የዮሐንስ 10፥30 ጥቅስ ከዘፍጥረት 1፥26 እና ከፊልጵስዩስ 2፥6 ጋር አጣምሮ ጥቅሶቹ በሙሉ ሰዎችን እንደሚመለከቱ ሲያስተምር ነበር። በኀይሉ ዮሐንስ ማብራሪያ መሠረት፣ “We are exactly like God.” [እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ሙሉ በሙሉ አንድ ዐይነት ነን]። ይህንንም እንደሚከተለው ያብራራዋል። “እኔና እግዚአብሔር አንድ ነን” በማለት ይጀምርና፣ እግዚአብሔር “‘ሰውን በመልካችንና በአምሳላችን እንፍጠር’ ማለቱ ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔርን እንድንመስል ያደርገናል” ይላል። ከዚያም ትምህርቱን በስፋት ወደ መተንተኑ ይገባል።

 

ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “አብን አሳየን” የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት፣ “እኔን ያየ አብን አይቷል” በማለት የመለሰበትን ዮሐንስ 14፥8ን የትምህርቱ ዋነኛ ዐምድ አድርጎ የሚወስደው ኀይሉ፣ ይህ አገላለጽ የኢየሱስን መለኮትነት የሚገልጽ ስላልሆነ አማኞች ሁሉ እንደዚህ ማለት እንደሚችሉ ያስተምራል። ተከታዮቹንም ይህንኑ መፈክር (ድጋም) በማስደገም፣ “ኮንፌስ” ሲያስደርጋቸው ታይቷል። ኀይሉ ዮሐንስ፣ “በእኔ አመለካከት ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ ደግሞ ሰው ነው። … ታላቅ ወንድማችን እንደዚያ ካለ፣ እኛም እንደዚያ ማለት እንችላለን” በማለት ጨምሮ ያስረዳል።

 

የኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅነት የኢየሱስ ሰው-ነት ማስረጃ አድርጎ ያቀረበው ኀይሉ ዮሐንስ፣ ወዲያው ማርሽ ይቀይርና የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት፣ የኢየሱስ መለኮነት ማስረጃ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ራሱንና ተከታዮቹን ከመለኮትነት ጋር ማስተካከሉን ይቀጥላል። “የልጁን መልክ እንድንመስል ወሰነን፤ በግማሽ አይደለም። 99 በመቶ አይደለም። መቶ በመቶ ነው። … ኢየሱስ ክርስቶስ አባቱን የሚመስል ከሆነ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ደግሞ የእኛም አባት ከሆነ፣ አባታችንን እንደምንመስል ምንም ጥያቄ የለኝም” በማለት።

 

እኛ እግዚአብሔርን የምንመስለው “ሙሉ በሙሉ” መሆኑንና እቅጩን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ መሆናችንን የሚያስተምረው ኀይሉ ዮሐንስ፣ በ2ኛ ጴጥሮስ 1፥4 ላይ ተመሥርቶ የሚከተለውን ሐተታ ያስከትላል። “ተወልደናል ብለን የምናስብ ከሆነ፣ … የመለኮት ባሕርይ ተካፋይ ሆነናል፤ partakers of the divine nature የሚለው ሐሳብ፣ ‘የተወሰነውን ተካፈልንʼ ለማለት ሳይሆን፣ ‘ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ባሕርይ ተላለፈብንʼ” ማለት መሆኑን ያስረዳል።

 

“ከእግዚአብሔር ባሕርይ አንዳንዶቹን ነው የተካፈልኩት” ማለትንም ግለ ሰቡ በአጽንኦት ይቃወማል። የዚህንም ምክንያት ሲያስረዳ፣ “እርሱ ብዙ ነገር ያፋልስብኛል። የተወሰነ ነገር ብቻ ከተካፈልን፣ መወለድ የሚባለው ነገር እውነት አይደለም። [አሊያ] እግዚአብሔር አልወለደንም። … ከተወለድኩ፣ የተወሰነ ባሕርይ omit [አጉድዬ] እወለዳለሁ የሚል እምነት የለኝም። … ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ተካፍያለሁ ብዬ ነው የማምነው። ያ እንደ እግዚአብሔር ያደርገኛል። … ‘የመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋይʼ የሚለውን ቃል፣ ‘በከፊል ተካፈልህʼ አይልም መጽሐፍ ቅዱስ። ሙሉ በሙሉ ነው የተካፈልሁት። … ያልተካፈልሁት ባሕርይ የለም። … እኔና አባቴ ተመሳሳይ ዝርያ ነው ያለን።” ከዚህም የተነሣ፣ “እግዚአብሔር ያለውን አለኝ፤ ከእርሱ በመወለዴ የእግዚአብሔር ባሕርይ በውስጤ አለ። መለኮታዊ ባሕርይን ተካፍያለሁ። ከተካፈልኩት ባሕርይ የተነሣ፣ እኔ እንደ አባቴ ነኝ። እኔና አብ አንድ ነን።” ሲል አቋሙን በግልጽ ያስቀምጣል።

 

በተጨማሪም፣ የእግዚአብሔር ልጅ መሆናችን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ምድብ ውስጥ እንደሚከትተን፣ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ መደብ እንደሚያደርገን ያስተምራል። “ሰው በእግዚአብሔር class [ምድብ] የሚኖር ነው። … ሰው በመልአክ class [ምድብ] አይደለም የሚኖረው። በመልአክ class [ምድብ] የማይኖርባቸው ሁለት ፋክተሮች [ምክንያቶች] አሉ። አንደኛ፣ ዝርያው፣ ዐይነቱ ራሱ አንድ አይደለም። ሰው ሰው ነው፤ መልአክ መልአክ ነው። ሁለተኛ፣ አኗኗራችንም አንድ ዐይነት አይደለም። የተፈጠርንበትም ዐላማ አንድ አይደለም። ሰው ግን በእግዚአብሔር class [ምድብ] ውስጥ ይኖራል። ማለቴ ምን ማለት ነው? ሰውና እግዚአብሔር የሚያመሳስላቸው ነገር ስላለ ነው። … [ምድቡን] አንድ ያደረገው፣ ሰው ከእግዚአብሔር የተገኘ ስለሆነ ነው። ሰው ከእግዚአብሔር ስለ ወጣ፣ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነ፣ አባትና ልጅ አንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ አባትና ልጅ ስለሆኑ፣ ‘ሰው በእግዚአብሔር [ምድብ] ይኖራልʼ ያልሁበት point [ነጥብ] አንዱ ይሄ ነው። ... ‘እኔ በአባቴ class [ምድብ] እኖራለሁʼ ብል ከአባቴ በወረስሁት ባሕርይ የተነሣ ነው።” ካለ በኋላ “የወጣነው ከእርሱ [ከእግዚአብሔር] ነው” በማለት ከአፈጣጠራችን በመነሣት የእግዚአብሔር አቻ ያደርገናል።    

 

ኀይሉ ዮሐንስ ይህን ካስረዳ በኋላም፣ “እግዚአብሔር እንደሚያዝዝ ማዘዝ እንችላለን። እግዚአብሔር የሚያውቀውን የማወቅ potential [ዕምቅ ዐቅም] አለን” ሲል ያክልበታል። የእግዚአብሔር ዝርያ እንደ ሆንን እና የእግዚአብሔር DNA [ዝርያ] በውስጣችን መኖሩን ያስገነዝባል። እግዚአብሔርን የሚመስለው መንፈሳችን (እውነተኛ ማንነታችን) በሥጋ የተገደበ ከመሆኑ በቀር፣ ያልተገደበ ሥልጣን ስላለን እግዚአብሔር በማንነት፣ በሥልጣንና በዕውቀት እኩያችን መሆኑን ያስተምራል። “Divine Order” በተሰኘው ስብከቱም፣ አዳም እግዚአብሔር የሚያውቀውን ያውቅ እንደ ነበር ከማስረዳት ይጀምርና፣ “የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው ለዕውቀቱ ገደብ የለውም” ወደ ማለት ይንደረደራል። “መለኮታዊ ባሕርይ እንዲያው ተሰጠን” ሲልም ይነግረናል። እንዲህ እንዲህ እያለ እያንዳንዳችን ዕጩ አምላክ (potential God) መሆናችንን “ያበስራል”።

 

ይህ የኀይሉ ዮሐንስ የዘወትር አስተምህሮ ነው። “Christological Concept” በሚለው ስብከቱም፣ “አዳምን ያየ እግዚአብሔርን አየ” ሲል ይፋ አድርጓል፤ ምክንያቱም፣ አዳምም እንደ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነውና! ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “[ኢየሱስ] የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው” ማለቱ (ቆላ. 1፥15)፣ ሁላችንንም የማይታየው አምላክ ምሳሌ እንደሚያደርገን ኀይሉ ዮሐንስ ያስተምራል። የዕብራውያን ጸሓፊም፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር “የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ” መሆኑን መናገሩም ከዚሁ ጋር እንደሚሄድ ግለ ሰቡ ገልጿል (1፥3)። በመሆኑም፣ አማኞች ሁሉ የእግዚአብሔር ክብር መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ነን! በብሉይ ኪዳንም፣ “እግዚአብሔር በአማልክት መካከል ቆመ” (መዝ. 82፥1) በሚል የተነገረው ስለ ሰዎች ነው፤ በኀይሉ ዮሐንስ አስተምህሮ መሠረት። “እግዚአብሔር በአማልክት ጉባኤ ቆመ የሚለው፣ ከእግዚአብሔር በተወለዱ፣ የእግዚአብሔር ባሕርይ ያለባቸውን የእግዚአብሔርን ልጆች ለማለት ነውና።”

 

እንደ ኀይሉ ዮሐንስ አስተምህሮ ከሆነ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ “ወልድ” የሆነው ከድንግል ማርያም ሲወለድ ብቻ ነው። ከዚያ በፊት ወልድ አልነበረም፤ አባት እንጂ። “ሰውን ከማዳን አንጻር ወልድ ሆነ።” አዲስ ኪዳን ስለ ኢየሱስ ጌትነት ቢናገርም፣ “ጌታ” የሚለው ሐሳብ የሚያሳየው፣ እግዚአብሔር ሰዎችን ከፈጠረ በኋላ፣ ምድርን … ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው” በማለት ካስተላለፈላቸው ሐሳብ ጋር አንድ ነው (ዘፍ. 1፥28)። ስለዚህም፣ “ኢየሱስ ጌታ የተባለው፣ በዘፍጥረት 1 ‘ግዙ ሲል ባረካቸውʼ በሚለው መሠረት ነው። ‘ጌታʼ ‘ንጉሥʼ የሚለውን ሐሳብ ካያችሁ፣ እርሱ ስለ ሰው ነው የሚያወራው” ሲል ያስተምራል። ስለዚህም አዳምና ሔዋን ምድርን እንዲገዙ የተቀበሉት እና እኛም ዛሬ በፍጥረት ላይ ያለን ሥልጣን ከኢየሱስ ጌትነት ጋር አንድ ነው።

 

ኀይሉ ዮሐንስ፣ “The Concept of Trinity” በሚለው ስብከቱም፣ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አባቶቻችን መሆናቸውን ይናገርና፣ ኢየሱስ ወልድ የሆነው ሰው ሆኖ ሲመጣ መሆኑን ያጸናል። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ለመባሉ ትርጕም ሲያስቀምጥም፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ማለት በሥጋ ውስጥ የሚኖር ጻድቅ ማለት ነው። [ኢየሱስ] ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ፣ ‘የእግዚአብሔር ልጅʼ ወደሚባል ማንነት ወረደ” ይላል። ከዚያም ስለ ሥላሴ አስተምህሮ ሲናገር፣ “የሥላሴ ምስጢር ብሎ ነገር የለም” ሲል ይደመድማል። (እግዚአብሔርን ዐውቆ እንደ ጨረሰ ሁሉ!) ነገረ ክርስቶስ (Christology)፣ ሥርዐት የያዘ ትምህርት ሆኖ በነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች በጥልቀት መሰጠቱንም ይቃወማል፤ “እንዴት አንድ subject [የትምህርት ዐይነት] ይወጣለታል ይሄ?” በማለት።

 

ኢየሱስ አብን መተረኩን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ዮሐ. 1፥18)። በኀይሉ ዮሐንስ አመለካከት፣ “አብን መተረክ ማለት ሰዎች [ምንጫቸውን] እንዲያውቁ ነው። [ምክንያቱም]፣ እግዚአብሔር ተተረከ አልተተረከ ምን ያደርግለታል?” በዚህ አካሄድ እግዚአብሔር፣ “ይህን የሚያደርገውም፣ ሰዎች ዐውቀው እንዲገዙለት” አይደለም። በመሆኑም፣ “አብ የሚለው ሐሳብ በተጠቀሰ ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር ማንነቱን ለመግለጥና ማንነቱ እንዲታወቅለት ሳይሆን ዐላማው፣ [ሰዎች] ምንጫቸውን እንዲያገኙ፣ ወላጅ አባታቸውን እንዲያውቁና ተመልሰው ወደ አባታቸው ቤት እንዲሰበሰቡ ነው” በማለት ያብራራል። በመጨረሻም፣ “የመጀመሪያው ወደ አባቱ የተመለሰ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” በማለት ይገልጻል።

 

ኀይሉ ዮሐንስ “Jesus, the Center of the Bible” በሚለው ስብከቱ ደግሞ፣ ጌታችን “መጻሕፍት ሁሉ ስለ እኔ ይናገራሉ” ማለቱን ያወሳና “መጻሕፍት ሁሉ ስለ ኢየሱስ የሚናገሩ ከሆነ፣ መጻሕፍት ሁሉ ስለ እኔና ስለ እናንተ ይናገራሉ። ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ ነውና” ሲል ከኢየሱስ ጋር አንድ አግዳሚ ላይ ያስቀምጠናል። በግለ ሰቡ አመለካከት፣ “የኢየሱስ ሕይወትና የሰው ልጅ ሕይወት የሚነጣጠል አይደለም፤ ለዚያ ነው ‘የሰው ልጅʼ ብሎ ራሱን የጠራው።” ጌታ ኢየሱስ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” (ማቴ. 28፥18) በማለት የገለጸው ሥልጣን፣ “ለሰው የተሰጠው ሥልጣን ነው። የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ነው።” ስለዚህም፣ “ከአሁን በኋላ ስለ እግዚአብሔር ሳይሆን፣ ስብከታችን የሰው ልጅ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን ነው” በማለት ኀይሉ ዮሐንስ የስብከቱን ዐላማ ያስቀምጣል። ኢየሱስን የምንወድ ከሆነም፣ የተነገረውን ቃል ትርጓሜ ሳንመራመር በዚህ መልኩ እንድንቀበል ያበረታታል።

 

ኀይሉ ዮሐንስ ይህን ሁሉ ካለ በኋላ፣ “ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነን ማለቴ አይደለም” በማለት “እግዚአብሔርን እንሆናለን” አለማለቱን ለማስረዳት ይጥራል። ነገር ግን “Exactly like God” ከሆንን፣ የእግዚአብሔርን ባሕርይ “አንዳችም ሳይቀር፣ ሙሉ በሙሉ” ከተካፈልን፣ እንደ ኢየሱስ “ጌታ እና ንጉሥ” መሆናችን ከተነገረን፣ “መደባችን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ መሆኑን” ከተረዳን፣ “እኔና አብ አንድ ነን” ብለን እንድናውጅ ከተበረታታን፣ “እንደ እግዚአብሔር ማዘዝና እንደ እግዚአብሔር ማወቅ እንደምንችል” እንዲሁም ለዕውቀታችን “ገደብ እንደሌለው” ከተረጋገጠልን በኋላ፣ “ከእግዚአብሔር ጋር እኩል አይደለንም” የሚለው መከላከያ ምን ትርጕም ይኖረዋል?  

 

ከዚህ በመቀጠል፣ ኀይሉ ዮሐንስ አስተምህሮውን የመሠረተባቸውን ጥቅሶች እና ምንባቦች ትክክለኛ ትርጓሜ እንቃኛለን። በመጀመሪያ፣ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ስለ መፈጠራችን (ዘፍ. 1፥26) እና የእግዚአብሔርን ባሕርይ ተካፋይ ስለ መሆናችን (2ጴጥ. 1፥4) እንወያያለን። ከዚያም፣ የኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅነት የተለያዩ ገጽታዎች ተመልክተን፣ በኢየሱስ እና በእኛ የእግዚአብሔር ልጅነት መካከል ያለውን ልዩነትና አንድነት እናጤናለን።

 

  1. የእግዚአብሔር መልክ እና ምሳሌ

እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በራሱ መልክና ምሳሌ መሆኑ እውነት ነው። እግዚአብሔር፣ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” ማለቱና “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” መባሉ ለዚህ ነው (ዘፍ. 1፥26-27)። የዘፍጥረት መጽሐፍ ስለ አዳም አፈጣጠር በሌላ ስፍራ ሲናገር፣ “ምሳሌ” የሚለውን ቃል ብቻ ይጠቀማል፤ “እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው” (5፥1)። አዳምም ከልጆቹ መካከል አንዱን የወለደው “በምሳሌው እንደ መልኩ” ነው (ዘፍ. 5፥3)።

 

ሰው በኀጢአት ከወደቀም በኋላ “የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ” መሆኑ አልቀረም። ስለዚህም፣ የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል (ዘፍ. 9፥6)። “በእርሱም [በአንደበታችን] እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን” የተባለውም ከውድቀት ከስንትና ስንት ዘመን በኋላ ነው (ያዕ. 3፥9)። የመካከለኛው ምሥራቅ ሌሎች ሃይማኖቶችም ይህንኑ መሳይ ግንዛቤ ነበራቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለአሕዛብ ሲሰብክ፣ “ከባለቅኔዎቹ አንዳንዶቹ ደግሞ ‘እኛ ዘመዶቹ ነንና’ ብለው እንደ ተናገሩ፣ ‘በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን’” በማለት የጠቀሰው ይህንን ነው (የሐዋ. 17፥28)።[2]

 

እስቲ ከዚሁ የሰው አፈጣጠር ጋር የሚያያዙ አንዳንድ ሐሳቦችን እንመልከት።

 

2.1  “መልክእናምሳሌሙሉ በሙሉ አንድ ዐይነትነትን (ልዩነት የለሽነትን) ያሳያሉን?

“መልክ” የሚለው ቃል በዕብራይስጡ “ጼሌም צֶלֶם” ሲሆን፣ ትርጕሙም ጥላ፣ ሥዕል፣ ምስል ማለት ነው።[3] ይህ ቃል በተለይ የጣዖት ምስሎችን ለማሳየት ሲውል፣[4] በብሉይ ኪዳን ውስጥ ለ17 ጊዜአት ያህል ጥቅም ላይ ውሏል። (እነዚህም ዘፍ. 1፥26፡27፤ 5፥3፤ 9፥6፤ ዘኁ. 33፥52፤ 1ሳሙ. 6፥5፡11፤ 2ነገ. 11፥18፤ 2ዜና 23፥17፤ መዝ. 39፥6፤ 73፥20፤ ሕዝ. 7፥20፤ 16፥17፤ 23፥14፤ አሞጽ 5፥26 ናቸው።) ቃሉ ከሞራላዊ፣ ከሥነ ምግባራዊ፣ ከአካላዊ ወይም ከባሕርያዊ ምስስል የትኛውን እንደሚያሳይ እርጠግኛ መሆን ባይቻልም፣[5] ጥቅም ላይ የዋለባቸውን ቦታዎች በማጤን፣ “ሙሉ በሙሉ አንድ ዐይነት” መሆንን እንደማያመለክት ግን መረዳት አይከብድም።  

 

ለምሳሌ፣ ፍልስጥኤማውያን የማረኩትን የቃል ኪዳን ታቦት ሲመልሱ፣ በእባጭ እና በአይጥ “ምሳሌ” የተሠሩ ወርቆችንም በእጅ መንሻነት አምጥተው ነበር (1ሳሙ. 6፥5፡11)። የወርቅ አይጦቹና እባጮቹ ከእውነተኞቹ አይጦችና እባጮች ጋር የሚመሳሰሉባቸውም የሚለያዩባቸውም ነገሮች አሉ። ቅርጻቸው ቢመሳሰልም፣ እውነተኞቹ አይጦችና እባጮች ከሥጋና ከደም፣ እነዚያኞቹ ደግሞ ከወርቅ የተሠሩ ናቸው። እውነተኞቹ አይጦች ሕይወት ሲኖራቸው፣ እነዚያኞቹ የላቸውም።

 

መዝሙረኛው ደግሞ፣ “ሰው እንደ ጥላ ይመላለሳል” ለማለት ይህንኑ ቃል ተጠቅሟል (39፥6)፤ “ጥላና አካል ሙሉ በሙሉ አንድ ዐይነት ናቸው፤ ልዩነት የላቸውም” ብሎ የሚከራከር ይኖር ይሆን? “በቀይ ቀለምም የተሣለችውን የከለዳውያንን ሥዕል፣ በናስ ላይም የተሣሉትን ሰዎች አየች” (ሕዝ. 23፥14)። እዚህም ጋ በእውነተኞቹ ሰዎችና በምስላቸው (በሥዕላቸው) መካከል ልዩነት ሊኖር መቻሉ ግልጽ ነው። “መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን አደቀቁ” (2ነገ. 11፥18)፤ “የርኩሰታቸውንም ምስሎች አደረጉባት” (ሕዝ. 7፥20)፤ “ከሰጠሁሽም ከወርቄና ከብሬ የተሠራውን የክብርሽን ዕቃ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ አድርገሻል” (ሕዝ. 6፥17)። “ጼሌም” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል የሚገኝባቸው እነዚህ ጥቅሶች እንደሚያሳዩን፣ በወርጅናሌውና በቅጅው (በምስሉ) መካከል የአንዳንድ ገጽታዎች ምስስል ቢኖርም፣ በሌሎች ገጽታዎች በኩል ደግሞ ልዩነት አለ። “መልክ” የሚለው ቃል “ሙሉ በሙሉ አንድ ዐይነት” መሆንን በጭራሽ አያሳይም።

 

በዘፍጥረት 1 ውስጥ “ምሳሌ” ተብሎ የተተረጐመው፣ “ዴሙት דּמוּת” የተሰኘ የዕብራይስጥ ቃልም ከዚሁ ጋር አብሮ ይሄዳል። “ዴሙት” አምሳያ፣ እንደ፣ አርአያ (model)፣ ቅርጽ የሚሉ ትርጓሜዎች አሉት።[6] ይህም ቃል በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም ላይ የዋለባቸው 25 ስፍራዎች የሚከተሉት ናቸው፤ ዘፍ. 1፥26፤ 5፥1፡3፤ 2ነገ. 16፥10፤ 2ዜና 4፥3፤ መዝ. 58፥4፤ ኢሳ. 13፥4፤ 40፥18፤ ሕዝ. 1፥5፡10፡13፡16፡22፡26፡28፤ 8፥2፤ 10፥1፡10፡21፡22፤ ዳን. 10፥16። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ግን፣ “አንዳችም ልዩነት የሌለው” እና/ወይም “ሙሉ በሙሉ አንድ ዐይነት” የሚል ትርጕም ሲሰጥ አንድም ጊዜ አናገኝም።  

 

እንዲያውም ብዙውን ጊዜ ዴሙት የሚለው ቃል ጥቅም ላይ የሚውለው የማይመሳሰሉ ነገሮችን በመጠቀም ንጽጽርን ለመፍጠር ነው፤ ለምሳሌ የሰዎችን ክፋት እና የእባብ መርዝን (መዝ. 58፥4)፤ የእግዚአብሔር ሰራዊት መሰባሰብን እና የብዙ ሕዝብ ድምፅን (ኢሳ. 13፥4)፤ የእግዚአብሔር መልአክን እና የሰው ልጅን (ዳን. 10፥16)። ነቢዩ ሕዝቅኤል ደግሞ ሰማያዊውን ራእይ በምድራዊ ነገሮች ለመመሰል ቃሉን በተደጋጋሚ ተጠቅሞበታል (ሕዝ. 1፥5፡10፡13፡16፡22፡26፡28፤ 8፥2፤ 10፥1፡10፡21፡22)።[7] የሚነጻጸሩት ነገሮች የሚመሳሰሉባቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን “በሁሉም ነገር አንድ ዐይነት” መሆንን የሚደግፍ ቃል አይደለም።

 

ለምሳሌ፣ የአዳም ሦስተኛ ልጅ (ሴት) ከአዳም ጋር ይመሳሰላል (ዘፍ. 5፥3)፤ ምናልባት የልጅየው የአፍንጫ ቅርጽ፣ የዐይኑና የጠጕሩ ቀለም፣ ቁመቱ፣ … ከአባቱ ጋር ይመሳሰል ይሆናል፤ ወይም የጠባይ መመሳሰል አላቸው።[8] አዳምና ልጁ በሆኑ ነገሮቻቸው ይመሳሰላሉ፤ በሆኑ ነገሮቻቸው ደግሞ ይለያያሉ። “በዐሥራ ሁለትም በሬዎች ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር” (2ዜና 4፥4)፤ መቼም በእውነተኛ በሬ እና ከናስ በተሠራ ምስለ በሬ መካከል ልዩነት መኖሩ የሚጠፋው ሰው አይኖርም። “ቊጣቸው እንደ እባብ መርዝ ነው” (መዝ. 58፥4)። የሰዎቹ ክፋት እንደ እባብ ሰዎችን ቢመርዝም፣ የእባብ መርዝ የተሠራበት ቊስ የሰዎቹ ቊጣ ከተሠራበት “ቊስ” ጋር አንድ ዐይነት እንዳልሆነ ማንም አይስተውም። ይህ ቃል ጥቅም ላይ ከዋለባቸው ቦታዎች አንዱ፣ “እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ?” ይላል (ኢሳ. 40፥18)። የዚህ ጥያቄ ምላሹ አሉታዊ ነው፤ በማንም አንመስለውም! ስለዚህ “ምሳሌ” የሚለውም ቃል “ሙሉ በሙሉ በሁሉም ነገር አንድ ዐይነት” ማለት አይደለም፤ መሳይነትን ብቻ ነው የሚያሳየው።

 

እንዲያውም ጼሌም እና ዴሙት የሚሉት ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዘፍጥረት 1፥26 ውጭ አብረው ውለው አያውቁም። ተወራራሽ ትርጕም ስላላቸው፣ አንዳቸውን በሌላኛቸው ምትክ መጠቀምም ይቻላል፤ ከዚህም የተነሣ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር”  ከተባለ በኋላ፣ የሚቀጥለው ቊጥር “ሰውን በመልኩ ፈጠረ” ብቻ ነው የሚለን (ዘፍ. 1፥26 እና 27)።

 

2.2  በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረው መንፈሳችን ብቻ ነውን?

ኀይሉ ዮሐንስና መሰሎቹ፣ የእግዚአብሔርን መንፈስነት ከተናገሩ በኋላ፣ “ሰው በሥጋ ውስጥ የሚኖር መንፈስ ነው” በማለት ያክሉበታል። ከዚያም በእግዚአብሔር አምሳልና መልክ የተፈጠረው የሰው ማንነት መንፈስ መሆኑን፣ እንዲሁም ሰው እና እግዚአብሔር በመንፈስነታቸው አቻ መሆናቸውን ሊያስረዱ ይጥራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሰው መንፈስ ብቻ በእግዚአብሔር አምሳል እንደ ተፈጠረ አያስተምርም። ሰው ሰው የሚሆነው ከነሁለንተናው (ሥጋ፣ ነፍስ፣ መንፈስ) ነውና።  

 

በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረው መንፈሳችን ብቻ ከሆነ፣ “በእግዚአብሔር መልክ ከፈጠራቸው በኋላ ወንድና ሴት አደረጋቸው” መባል ነበረበት። መጽሐፍ ቅዱስ ግን፣ “በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ነው የሚለው (ዘፍ. 1፥26-27)። “ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር” መሆኑ መነገሩም ከዚሁ ጋር ሊወሰድ ይችላል (1ቆሮ. 11፥7)። “የሰው መንፈስ ጾታ አለው” ካላልን በቀር።

 

“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር ዐፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ” የተባለው የአዳምን የአፈጣጠር ቅደም ተከተል ይናገራል (ዘፍ. 2፥7)። ከዐፈር የተበጀው ቊሳዊ አካላችን የማንነታችን አንዱ ክፍል መሆኑን ከዚህ አገላለጽ እንገነዘባለን። “አቤቱ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ጭቃ ነን፤ አንተም ሠሪያችን ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን” (ኢሳ. 64፥8) መባሉም ከዚህ ሐሳብ ጋር ዝምድና እንጂ ጠብ የለውም።

 

በተጨማሪም እግዚአብሔር፣ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” ያለው፣ የሰውን ሥጋ ከዐፈር ከፈጠረ በኋላ ለመሆኑ አንዳችም ማስረጃ የለም። ኢ-ቊሳዊ አካላችን (መንፈሳችን ወይም ነፍሳችን) ብቻ ተነጥሎ በእግዚአብሔር መልክ አልተፈጠረም፤ ሰው ያለ ሥጋው (ያለ ቊሳዊ አካሉ) ሙሉ አይደለምና። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረው ሙሉው ሰው እንጂ መንፈሱ ብቻ አይደለም! እግዚአብሔር ሥጋዊ አካል ባይኖረውም፣ ሥጋዊ አካላችን የእግዚአብሔርን ባሕርይ የሚገልጥበት የራሱ መንገድ ይኖረዋል። (ለምሳሌ ማየት፣ መስማት፣ መናገር በሥጋዊ አካላችን የሚፈጸሙ ናቸው፤ እግዚአብሔርም ደግሞ ማየት፣ መስማት፣ መናገር ይችላል!)[9]

 

በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረው መንፈሳችን ብቻ ላለመሆኑ፣ የሰውን አሟሟት በአስረጅነት ማቅረብ ይቻላል። ሰዎች መግደል የሚችሉት ሥጋን ነው፤ ነፍስን/መንፈስን መግደል አይችሉም። ጌታችን፣ “ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ” ብሏልና (ማቴ. 10፥28)። በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር፣ “የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል (ዘፍ. 9፥6)። ሰዎች ሥጋን ብቻ መግደል (ደምን ማፍሰስ ብቻ) መቻላቸው ከታወቀ፣ የሰውን ደም በእግዚአብሔር መልክ ከተፈጠረ “ነገር” ጋር ምን አገናኘው ታዲያ? ምክንያቱ ግልጽ ነው፤ በእግዚአብሔር መልክ መፈጠራችን ሁለንተናችንን እንጂ መንፈሳችንን ብቻ የሚመለከት አይደለም! ሰው በአካል ተፈጥሮአል፤ ይህም አካል የመለኮት፣ የእግዚአብሔር ክብር ተንጸባርቆበታል።

 

ሰው በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረው ሁለንተናው ነውና (ይህ ሲባል ግን አምላክ እንደኛ ቊሳዊ አካል አለው ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል!) ኀጢአት ሁለንተናውን ነው ያናጋው። ሰው በኀጢአት ሲወድቅ፣ ንጹሕ የነበረው ሥጋውም ሆነ መንፈሱ ቆሸሸ። በመንፈሱም በሥጋውም ሞት መጣበት። የእግዚአብሔር መልክና አምሳል ከሰው ላይ ባይጠፋም፣ የተበረዘ፣ የተከለሰ፣ የተበላሸ ነገር መኖሩ እውነት ነው። የሰው ሥጋዊም መንፈሳዊም ንጽሕና ረከሰ። ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ልብሱ ወልቆ ተራቆተ። ኢየሱስ ክርስቶስም የመጣው በውድቀት ጊዜ የተበላሸውን የሰው ልጅ ሁለንተና ሊያድስ እንጂ መንፈሳችንን ብቻ ሊፈውስ አይደለም፤ የሥጋችንም ቤዛ እርሱ ነው (ሮሜ 8፥23)! ስለዚህም ልጁን ለመምሰል የሚታደሰው ይኸው ሁለንተናዊ ማንነታችን ነው። እኛ ሥጋና መንፈስ (ነፍስና መንፈስ ወይም ኢ-ቊሳዊው በአንድ ላይ) ነን። እስከ ሞትም፣ ከትንሣኤ በኋላም ይህ አንድነት ይቀጥላል።

 

2.3  የ“መልክ” እና “ምሳሌ” ትርጓሜ አማራጮች

ኀይሉ ዮሐንስ “እኛና አብ አንድ ነን” ለማለት፣ በአብ ምሳሌ መፈጠራችንን በዋቢነት ይጠራል። ይህ ግን ትክክል አይደለም። የምንባብ ክፍሉ አብን ነጥሎ አይናገርም። “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” የሚለው ዕቅድ፣ በእግዚአብሔር አካላት መካከል የተደረገ ምክክር ነው። የተፈጠርነው በአርአያ ሥላሴ ነው።

 

ሰው በአርአያ ሥላሴ መፈጠሩን ቅዱሱ መጽሐፍ ሲናገር፣ ሰዎች በእግዚአብሔር መልክ የመፈጠራቸው አንዱ ማሳያ እርስ በርስ መዋደድ እና እርስ በርስ መያያዝ ያለባቸው መሆኑ ነው። ግለኛነት የእግዚአብሔር መልክ አይደለም። “እኛ” የሚል አምላክ ፈጥሮናልና፣ እኛም “እኛ” ባዮች መሆን ይጠበቅብናል። እግዚአብሔር አንድን ሰው ከመፍጠር ይልቅ ሁለት ሰዎችን የፈጠረው ለዚህ ነው። ከእኔነት ይልቅ እኛነት ተፈጥሯዊ ባሕርያችን ነው። የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሞያዎች፣ ማኅበራዊ ፍጥረት መሆናችንን በማተታቸው አልተሳሳቱም። በአርአያ ሥላሴ መፈጠር ትርጕሙ ይህ ሊሆን ይችላል።[10]

 

ሰው በእግዚአብሔር መልክ መፈጠሩ፣ ከተቀሩት እንስሳት የበላይ መሆኑንም ያሳያል። ሰው እግዚአብሔርን ወክሎ፣ ፍጥረትን ይገዛል፤ በዚህም እግዚአብሔርን ይገልጣል። “ሰው በእግዚአብሔር መልክ ተፈጠረ ማለት፣ ሰው እግዚአብሔርን ይመስላል እንዲሁም እግዚአብሔርን ይወክላል ማለት ነው።”[11] ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ “ሰውን በመልካችን እንፍጠር” ካለ በኋላ፣ ሰው እግዚአብሔርን ወክሎ ፍጥረትን መግዛት እንዳለበት ያብራራልና፤ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፣ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፣ በምድር የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ …” (ዘፍ. 1፥26-28)። መዝሙረኛውም፣ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጐበኘው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው? ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፤ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው። በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛህለት” ሲል ዘምሯል (መዝ. 8፥4-6)።  

 

ከእነዚህም በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ “ምሳሌ” እና “መልክ” ምን ማለት እንደ ሆነ ለመረዳት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። መልክና ምሳሌ፣ ሰው እግዚአብሔርን እንዲያውቅ አእምሮአዊነትን እንደ ታደለ፣ መልካምንና ክፉን መምረጥ እንዲችል ነጻ ፈቃድ እንደ ተሰጠው፣ ከበታቹ ያሉ ፍጥረታትን ለማስተዳደር የሚያስፈልገውን ኀይል እንደ ታጠቀ፣ የሚያሳዩ ቃላት ስለ መሆናቸው ግንዛቤ ተወስዷል።[12] በተጨማሪም፣ ሰው ሥነ ምግባራዊ ተፈጥሮ ያለው መሆኑን ሊያስረዱም ይችላሉ።

 

መልክ እና ምሳሌ፣ አዳም ሲፈጠር የነበረውን ወርጅናሌ ንጽሕናም ያሳያሉ። እግዚአብሔር ሰዎችን ከፈጠረ በኋላ፣ ይህ “እጅግ መልካም ነበረ” ማለቱ (ዘፍ. 1፥31) እና “እግዚአብሔር ሰዎችን ቅኖች አድርጎ  እንደ ሠራቸው” መነገሩ (መክ. 7፥29) ለዚህ ምስክር ነው፤ ይህም የእግዚአብሔርን ሞራላዊ መልክ ያሳያል።[13] በእርግጥ፣ የመልክና የአምሳል ትርጓሜዎችን በእነዚህ ብቻ ገድቦ ማስቀመጥ አግባብነት ላይኖረው እንደሚችል እዚህ ጋ መስተዋል አለበት።

 

ከዚህ ውጭ ግን ሰውና እግዚአብሔር አንዳችም ልዩነት የሌላቸው ተመሳሳዮች መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም። የሚመሳሰሉባቸው ገጽታዎች የመኖራቸውን ያህል፣ በጭራሽ የማይመሳሰሉባቸው ገጽታዎችም ሞልተዋል። ሰው ከእግዚአብሔር መውጣቱንም ሆነ ሰው ከእግዚአብሔር መወለዱን የዘፍጥረቱ ታሪክ በየትኛውም ስፍራ አይነግረንም። ሰውና እግዚአብሔርም አንድ አይደሉም። ሰው ሰው ነው፤ እግዚአብሔር ደግሞ መለኮት!

 

2.4  ከእግዚአብሔር ጋር የምንለያይባቸውን ገጽታዎች ከጥንተ ፍጥረት ተረክ ማግኘት ይቻላልን?

እንዴታ! የዘፍጥረቱ ተረክ፣ ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ መፈጠሩን ብቻ ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ልዩነት በግልጽ ያስቀምጣል። ለምሳሌ፣

 

  • እግዚአብሔር ፈጣሪ ነው፤ ሲፈጥር ከምንም (“እም ኀበ አልቦ” ex nihilo) ነው የፈጠረው (ዘፍ. 1፥1)። እኛ ፍጡራን ነን፤ አንድን ነገር ከምንም (something from nothing) ልንፈጥር አይቻለንም። ከዳንንም በኋላ አዲስ ፍጥረት እንጂ አዲስ ፈጣሪ አልሆንንም (2ቆሮ. 5፥17)።
  • እግዚአብሔር ሕይወት ነው፤ ሕይወት ሰጭ ነው። እኛ ደግሞ ሕይወትን ተቀባዮች ነን (ዘፍ. 2፥7)።
  • እርሱ “እግዚአብሔር አምላክ” ነው (ዘፍ. 2፥4፡5፡7፡8፡9፡16፡18፡19፡21)፤ እኛ ደግሞ ሰዎች ነን (ዘፍ. 1፥26-27፤ 2፥7-8)። ሰው ሰው ነው፤ እግዚአብሔርም መለኮት። መደባችን ይለያያል።
  • እግዚአብሔር መጀመሪያ የለውም፤ የመጀመሪያ (የጊዜ) አስገኝ እርሱ ራሱ ነው። እኛ ደግሞ መጀመሪያ፣ መነሻ አለን።
  • እግዚአብሔር መልካምንና ክፉን ያውቃል፤ “ይህ ነገር መልካም፣ ይህ ደግሞ ክፉ ነው” ባዩ ራሱ ነው። መሪ፣ መንገድ ጠቋሚና አዛዥ አያውቅም። ደንጋጊ የለበትም። ትእዛዙ ሲጣስም ቅጣት ያስተላልፋል። ሰው ደግሞ ሲፈጠር ጀምሮ በራሱ ድንጋጌ፣ “ይህ ነገር መልካም ነው፤ ይህኛው ደግሞ ክፉ” ማለት አይችልም፤ መልካምንና ክፉን አያውቅም። የእግዚአብሔርን ድንጋጌና ትእዛዝ ነው የሚከተለው፤ ካልታዘዘ ቅጣት ይከተለዋል (ዘፍ. 2፥16-17)። እባቡ ለሔዋን ያቀረበላት ፈተና በአንድ በኩል እዚህ ላይ የተንጠለጠለ ነበር፤ “እንደ እግዚአብሔር መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ … ነው” የሚል (ዘፍ. 3፥5)። ይህ ልዩነት እውነት እንደ ነበር፣ “እግዚአብሔር አምላክም አለ፤ እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን በማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ከሚለው ንግግር እንማራለን (ዘፍ. 3፥22)። [14]
  • ሰው ፈተና ሲቀርብለት፣ በፈተናው መውደቅም ሆነ ማለፍ ይቻለዋል፤ እግዚአብሔር ግን አይወድቅም።

 

ታዲያ ቢያንስ ቢያንስ በእነዚህ ጕዳዮች ልዩነት እያላቸው፣ ሰዎች `exactly like God` ሊሆኑ ይችላሉን? በጭራሽ!

 

“በልዑል እመሰላለሁ” ያለው ሰይጣንም ሆነ “እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ” የተባሉት የሰው ልጆች፣ ይህን ክጃሎት እውን ለማድረግ በራሳቸው ላይ ያመጡት አሳርንና ፍዳን እንጂ እርሱን መሆን አልነበረም። በአጠቃላይ “እንደ እግዚአብሔር መሆን” የሚለው ተምኔት፣ የሐሰት አባት ከሆነው ከሰይጣን ዲያብሎስ የተገኘ ውሸት ነው (ዘፍ. 3፥5፤ ኢሳ. 14፥14፤ ዮሐ. 8፥44)።

 

  1. “የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች”

ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ “ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፣ … የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን” ሲል ጽፏል (2ጴጥ. 1፥4)። እነ ኀይሉ ዮሐንስ፣ “የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች” የሚለውን ሐሳብ፣ የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ባሕርይ ምንም ሳያስቀሩ ሁሉንም መካፈል አድርገው ይተረጕሙትና ከእግዚአብሔር ጋር አንዳችም ልዩነት እንደሌለን ይናገራሉ። ጥቅሱ ግን ይህንን ሐሳብ እንዳልተሸከመ ከዚህ ቀጥለን እንመለከታለን።

 

“ተካፋይ” የሚለው ቃል በግሪክ “ኮይኖኖይ κοινωνοὶ” ሲሆን፣ ኮይኖኖስ (κοινωνός) እና ኮይኖንያ (κοινωνὶα) ከሚሉት ቃላት ጋር ቤተ ሰብ ነው። ይህም ተባባሪነትን፣ አብሮ ሠራተኝነትን፣ የሥራ ጓድነትን፣ ባልንጀርነትን፣ ማኅበረተኝነትን፣ አንዳንድ ነገሮችን (ለምሳሌ ሥቃይንና መጽናናትን መካፈልን) የሚያሳይ ቃል ነው።[15] “ኮይኖኖይ” በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለ10 ጊዜያት ያህል ጥቅም ላይ ውሏል፤ እነዚህም ማቴ. 23፥30፤ ሉቃ. 5፥10፤ የሐዋ. 2፥42፤ 1ቆሮ. 10፥18፡20፤ 2ቆሮ. 1፥7፤ 8፥23፤ ፊልሞን 1፥17፤ ዕብ. 10፥33፤ 1ጴጥ. 5፥1፤ 2ጴጥ. 1፥4 ናቸው።

 

ቃሉ በስፋት ጥቅም ላይ የዋለው ትብብርን እና ባልንጀራነትን ለማሳየት ቢሆንም፣ “የአጋንንት ማኅበረተኛነት”ን ለማሳየት ሐዋርያው ጳውሎስ ሁለት ጊዜ ተጠቅሞበታል (1ቆሮ. 10፥18፡20)። ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ ለጣዖት የታረደውን ሥጋ የሚበሉ አማኞች ከአጋንንት ጋር “አንድ አካል፣ አንድ አምሳልነታቸውን” እየተናገረ እንዳልሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ግሪክኛው ቃል፣ “ሙሉ በሙሉ አንድ ዐይነት” የሚል ትርጕም የለውምና!

 

ኀይሉ ዮሐንስን ጨምሮ ሌሎችም፣ “አማርኛው ‘የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች’ የሚለውን፣ እንግሊዝኛው ‘partaker of the divine nature’ ይለዋል” ማለትን ያዘወትራሉ። እውነታቸውን ነው፤ (ለምሳሌ ASV, ESV, KJV, NASB, RSV)። ታዲያ፣ partaker ምን ማለት ነው? “ሙሉ በሙሉ፣ ያለ አንዳችም ልዩነት” መመሳሰልን ያሳያልን? በጭራሽ! ለምሳሌ፣ Merriam-Webster Dictionary ቃሉን፣ “to have some of the qualities of something.” በሚል ነው የሚፈታው፤ “የአንድን ነገር ከፊል ወይም ጥቂት ገጽታዎችን መካፈል” ማለት ነው። በርካታ መዛግብተ ቃላት፣ በግብዣ፣ በስፖርታዊ ውድድሮች ወይም እነዚህን በሚመስሉ ጕዳዮች ላይ ተሳትፎ ማድረግን የሚያሳይ ቃል አድርገው ነው የሚፈቱት። ስለዚህ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ የመለኮት ባሕርይ ተካፋይነትን ሲናገር፣ ሙሉ በሙሉ፣ ያለ አንዳችም ልዩነት፣ exactly ከእግዚአብሔር ጋር መመሳሰላችንን ለማስተማር አይደለም።

 

የእግዚአብሔርን ባሕርይ የምንካፈለው ከምን አኳያ እንደ ሆነ ከምንባብ ክፍሉ ዐውድ በመነሣት መረዳት አስቸጋሪ አይደለም። ጥቅሱ እንደሚከተለው ይነበባል፤ “ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፣ … እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን”። ሌሎች የአማርኛ ትርጕሞችን መመልከት ሐሳቡን ይበልጥ ለማስተዋል ያግዛል። “ከክፉ ምኞት የተነሣ በዓለም ካለው ምግባረ ብልሹ ሕይወት አምልጣችሁ ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ በእነዚህ ነገሮች አማካይነት እጅግና ታላቅና ክቡር የሆነውን ተስፋ ሰጥቶናል” (አ.መ.ት)። “የመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንድንሆንም የተትረፈረፈ ስጦታውንና ድንቅ በረከቱን ሊያድለን ታላላቅና ውድ ተስፋዎችን ሰጥቶናል። ይህም መለኮታዊ ኀይል ከፈቃደ ሥጋ ምኞትና በአካባቢያችሁ ካለው የዓለም ብልሹ ሕይወት እንድትጠበቁ የሚያስችላችሁ ነው” (ሕያው ቃል)።

 

እንግዲህ ጥቅሱ እንደሚነግረን፣ እግዚአብሔርን የመምሰል (መለኮታዊ ባሕርይን የመካፈል) ተስፋ ተሰጥቶናል፤ ይህም ተስፋ ከክፉ ምኞት፣ ከምግባረ ብልሹነት፣ ከፈቃደ ሥጋ ምኞት እንድናመልጥ (እንድንጠበቅ) የሚያግዝ ነው። ተስፋው የተጋመደው ከቅድስና እና ከንጽሕና ጋር ነው ማለት ነው፤ ከእግዚአብሔር የምንካፈለው የባሕርይ መገለጫም ትይይዙ ከዚህ ጋር ነው። ይህን እንድናደርገው ደግሞ ቀድሞውኑም ታዝዘናል (ለምሳሌ 1ጴጥ. 1፥15-16)። በሁሉ ነገር፣ ሁል ጊዜ፣ ሙሉ በሙሉ፣ ያለ አንዳች ልዩነት ከእግዚአብሔር ጋር አንድ መሆናችንን ከቶውኑም ክፍለ ምንባቡ አይናገርም።

 

ለነገሩማ ይህም ቢሆን ተስፋ እንጂ፣ ሰው ሆነን በተፈጠርንበት ወቅት ተፈጽሞ ያለቀ ጕዳይ እንዳልሆነ መረዳት አይቸግርም። በተጨማሪም የእግዚአብሔርን ባሕርይ ሙሉ በሙሉ የወረስን ከሆነ፣ “እግዚአብሔርን ምሰሉ” (ኤፌ. 5፥1 - አ.መ.ት) ተብለን የታዘዝነው ለምንድን ነው? የሆንነውን ነገር ለመምሰል ለምን እንጠየቃለን? ይህ የሚያስገነዝበን፣ ጭራሹኑ እግዚአብሔርን ያልመሰልንባቸው ገጽታዎች መኖራቸውን ነው!

 

ከዚህ የተነሣ እኛና እግዚአብሔር አንድ አይደለንም። ሐዋርያትም ሆኑ እነርሱን ከተከተሉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል “እኔና አብ አንድ ነን” በማለት የተናገረ ወይም የጻፈ አንድም ሰው የለም፤ “እኔና አብ አንድ ነን” ያለው በባሕርይው መለኮት፣ ማለትም ከአብ ጋር አንድ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ከእርሱ በቀር ማንም ይህንን አላለም! ፊልጵስዩስ 2፥6ም “እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ” (አ.መ.ት) በማለት የሚገልጸው ቀድሞም በማንነቱ እግዚአብሔር የሆነውን ኢየሱስን እንጂ ሰውን ሁሉ አይደለም። ከዚህ አኳያ፣ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም በእግዚአብሔር መልክ (form) (“ሞርፌ” μορφή) ሊኖር አይችልም።[16] እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለምና!

 

እግዚአብሔር መንፈስ ነው። እናም በሁሉ ስፍራ ይኖራል። እርሱ ምንም እንኳ ካልሆነ ነገር ምንምን መፍጠር ይችላል፤ ኀይሉና ችሎቱ መጠንና ልክ የሌለው ነው፤ ሥልጣኑ አይመረመርም። ጥበቡና ዕውቀቱ ሊለኩትም የማይታሰብ ነው። ከእርሱ ባሕርያት መካከል በእኛ ውስጥ የሌሉት የትየለሌ ናቸው። መንፈሳዊ ኅላዌውን ከሚያሳዩት ባሕርያት መካከል በእኛ ዘንድ ያሉት ጥቂቶቹም ቢሆኑ፣ በኀጢአት ተበክለው እንደ ተሰባበረ መስተዋት ነው የሚያሳዩት።

 

ከዚህ ይልቅ እግዚአብሔርን የምንመስልባቸው ገጽታዎች እና የማንመስልባቸው ገጽታዎች መኖራቸው ልከኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ነው። እርሱን የምንመስልባቸው (መምሰል የምንችልባቸው) ዘርፎች “ተወራሲ የእግዚአብሔር ባሕርያት (Communicable Attributes)” በመባል ሲታወቁ፣ እርሱን መምሰል የማንችልባቸው ደግሞ “ኢተወራሲ ባሕርያት (Incommunicable Attributes)” ተብለው ይታወቃሉ።[17] መውረስ፣ መካፈል የምንችለውም የእግዚአብሔርን የባሕርይ መገለጫዎች እንጂ የእግዚአብሔርን ማንነት አይደለምና መለኮታዊ ባሕርያቱን ሙሉ በሙሉ እንደምንካፈል ማሰብ፣ “እግዚአብሔር እንሆናለን፣ እንመለካለን” ከማለት ጋር ልዩነት የሌለው ኑፋቄ ነው።[18] እርሱን የምንመስለው፣ የባሕርይው ተሳታፊዎች፣ ማኅበረተኞች የምንሆነው፣ በእኛ ውሱንና ፍጡራዊ ማንነት ሊንጸባረቁ በሚችሉት ባሕርያቱ ብቻ ነው። ጨርሶውኑ የማንሆናቸው ባሕርያቱ፣ የራሱ ብቻ የሆኑት ባሕርያቱ የእርሱ ብቻ ናቸው። አሁንም ወደፊትም፣ ለዘላለምም አንካፈላቸውም።

 

  1. የእግዚአብሔር ልጅ/ የእግዚአብሔር ልጆች

አባትነት የተለያዩ ገጽታዎች ሊኖሩት ይችላል። ለምሳሌ፣ የሥጋ አባቴ ለእኔ የቀለም አባቴም ነው፤ ፊደል ያስቈጠረኝ፣ ከመጻሕፍት ጋር ያዛመደኝ እና ለንባብ አርአያ የሆነኝ እርሱ ነውና። መንፈሳዊ አባቴም እርሱ ነው፤ በልጅነቴ የክርስትናን ሀሁ ከማስተማሩም ባሻገር፣ ሳድግም እርሱ መጋቢ በሆነባት ቤተ ክርስቲያን በአባልነት ኖሬአለሁ። አባቴ በሥጋ ሳይወልዳቸው አሳዳጊ አባት የሆናቸው፣ የቀለም አባት እንጂ መንፈሳዊ አባት ያልሆናቸው፣ መንፈሳዊ አባት ሆኗቸው የቀለም አባት ያልሆናቸው ሌሎች ልጆችም አሉት።

 

ይህም በመሆኑ እኔና አባቴ በተፈጥሮ ዝርያ (DNA) ተመሳሳዮች ነን። መንፈሳዊ አቋማችን ተመሳሳይነት አለው፤ ዕውቀትን በመፈለግ ረገድም እንደዚያው ነን። በዝርያ ከአባቴ ካልተከፈሉት፣ ነገር ግን በመንፈሳዊነት እና በዕውቀት ረገድ የእርሱ ከሆኑት ልጆቹ ጋር ሲነጻጸር የእኔ የእርሱ ልጅነት እጅግ የላቀ ደረጃ አለው፤ ልዩ ነው! እርሱ የገዛ አባቴ፣ እኔም የገዛ ልጁ ነኝ።

 

ከዚህ አኳያ ስናየው፣ የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት የተለያዩ ገጽታዎች አሉት።[19] የእግዚአብሔር ልጅነቱ በአንደኛው ገጽታ መለኮትነቱን ያረጋግጣል፤ የእኛ ልጅነት ከዚህ ልጅነት ጋር ከቶውኑ በአቻነት አይቀርብም። ሌላኛው የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ደግሞ፣ ሰው ከመሆኑ ጋር የተሳሰረ ነው። ኀይሉ ዮሐንስና መሰሎቹ ግን፣ የኢየሱስ ክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅነት እና የአማኞችን የእግዚአብሔር ልጅነት ያለ አንዳችም ልዩነት ሁል ጊዜም አንድና አቻ ያደርጉታል። ስለዚህም የእኛንና የእርሱን ልጅነት አንድነት እና ልዩነት አሁን እናጠናለን። በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ አካል ያለው፣ አንድ እኔታ (person) መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም!

 

4.1  የእግዚአብሔር ልጅነት እና አምላክነት (እግዚአብሔርነት)

ሐዋርያው ዮሐንስ፣ “ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ ዕቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ተረከው” (ዮሐ. 1፥18 - አ.መ.ት.) በማለት ጽፏል። “አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ” እና “በአብ ዕቅፍ ያለው” የሚሉት አገላለጾች የእግዚአብሔር ልጅነቱንና አምላክነቱን በአንድ ገምደውታል። ይህም የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ትርጓሜው አምላክነት መሆኑን በማያሻማ መንገድ ያስረዳል።

 

በዚህ ክፍል “አንድያ ልጅ” ተብሎ የተተረጐመው፣ በግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኖገኔስ ሁዮስ (μονογενὴς υιος)” የተባለው ነው። ሁዮስ “ልጅ” ማለት ሲሆን፣ “ሞኖስ” እና “ጌኖስ” ከሚሉት ቃላት ጥምረት የተፈጠረው ሞኖገኔስ ደግሞ፣ “በዐይነቱ የተለየው፣ የተለየ መደብ ያለው፣ ልዩ የሆነው፣ መሳይ የሌለው” (“pertaining to being the only one of its kind within a specific relationship” and “pertaining to being the only one of its kind or class, unique (in kind)” ማለት ነው።[20] ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን ቃል 5 ጊዜ ተጠቅሞበታል (1፥14፡18፤ 3፥16፡18፤ 1ዮሐ. 4፥9)። ቃሉ የክርስቶስን ልጅነት ከአዳም (ሉቃ. 3፥28)፣ ከመላእክት (ኢዮብ 1፥6) ወይም ከአማኞች የተለየ ያደርገዋል (ዮሐ. 1፥12)፤[21] የኢየሱስን ዐይነት ልጅነት ያለው ማንም (በሰማይም ሆነ በምድር) እንደሌለ ይመሰክራል። ጌታ ኢየሱስ አንዱና ብቸኛው ወልደ እግዚአብሔር ነው! የእግዚአብሔር “የባሕርይ ልጅ” የሚባለውም ለዚህ ነው! ዝርያው ከሁሉ ልዩ ነው!

 

ይህ ልዩና መሳይ የሌለው ልጅ፣ በማንነቱ አምላክ ነውና፣ “እግዚአብሔር የበኵር ልጁን ወደ ዓለም በላከ ጊዜ፣ ‘የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይስገዱለትʼ” ተብሏል (ዕብ. 1፥6፤ የ1997 ትርጕም)። ደቀ መዛሙርቱም፣ “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሰግደውለታል (ማቴ. 14፥33)። ስግደት ደግሞ የአምልኮ አንዱ ክፍል መሆኑ ይታወቃል። በዚህም፣ ስግደትን (ከመላእክትም ሆነ ከሰው) መቀበሉ እና የእግዚአብሔር ልጅነቱ ቊርኝት እንዳላቸው እናስተውላለን። ይህም አምላክነት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፤ ለፍጡር መስገድ በአዲስ ኪዳን ክፉኛ የተከለከለ ነውና (ማቴ. 4፥10፤ ሉቃ 4፥8፤ ራእይ 19፥10፤ 22፥9)። ወንጌላቱ እንደሚነግሩን፣ ለምጻሙ ሰው (ማቴ. 8፥2)፣ ኢያኢሮስ (9፥18)፣ ሲሮፊኒቃዊቷ ሴት (ዮሐ. 9፥38)፣ ሌጌዎን (ማር. 5፥6)፣ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደው ሰው (ዮሐ. 9፥38) ለኢየሱስ ሰግደዋል።[22]  

 

መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሰዎችና አጋንንት ለኢየሱስ ክርስቶስ ስግደትን ስለ ማቅረባቸው ወይም መላእክት ለልጁ እንዲሰግዱ ስለ መታዘዙ ለመናገር የተጠቀሙበት የግሪክ ቃል “ፕሮስኩኔዎ προσκυνέω” ነው። ለእግዚአብሔር ብቻ ስግደት የተገባ እንደ ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የተናገረውም በዚሁ ግሪክኛ ቃል ነው (ማቴ. 4፥10፤ ሉቃ 4፥8፤ ራእይ 19፥10፤ 22፥9)። “ፕሮስኩኔዎ” የሚለው ቃል ማምለክ፣ አክብሮት መስጠት፣ እግር ሥር መውደቅ፣ መሬት ተደፍቶ እግርን ወይም የልብስን ጫፍ መሳም የሚሉ ትርጓሜዎች አሉት።[23] መላእክትና ሰዎች ለኢየሱስ የሚያደርጉትን ስግደት፣ እንግሊዝኛ ትርጕሞች “worship” በማለት አቅርበውታል፤ ለኢየሱስ የሚደረግ ስግደት አምልኮ ነውና! ኢየሱስ በእግዚአብሔር ልጅነቱ ስግደት ከቀረበለት፣ የእግዚአብሔር ልጅነቱ መለኮትነት መሆኑን ያሳየናል። ይህም የእኛ የእግዚአብሔር ልጅነት ከእርሱ ልጅነት ጋር አንድ እንዳልሆነ ያስገነዝባል።

 

አጋንንትም የኢየሱስን ማንነት ተረድተው፣ “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ” በማለት ጮኸው ይወጡ ነበር (ማቴ. 8፥29)። “ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል”  ከሚለው የደቀ መዛሙርቱ ዘገባም፣ አጋንንት በስሙ ይታዘዙ እንደ ነበር እንማራለን (ሉቃ. 10፥17)። ስለዚህ አጋንንትን ያስወጣው የእግዚአብሔር ልጅነቱ ከእኛ የእግዚአብሔር ልጅነት የተለየ ነው። የእርሱ ስም ጕልበት አለው! የእኛ ስም ግን ጕልበት የለውም፤ አጋንንትንም አያስወጣም!

 

ጌታ ኢየሱስ በራሱ ሞት እና ትንሣኤ ላይ ሥልጣን እንዳለው በመናገሩ፣ አይሁድ እንዳበደና ጋኔን እንዳለበት ሰው ቈጥረውታል። “ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ” (ዮሐ. 10፥17-20)። ራሱ ፈቅዶ በወሰነው ጊዜ ነፍሱን ሰጠ እንጂ፣ ጊዜው ከመድረሱ በፊት ጌታ ኢየሱስን ማንም ሊይዘው አይችልም ነበር (ዮሐ. 7፥30፤ 8፥20)። በሞቱ ላይ ሥልጣን ነበረውና ሰዓቱ ሲደርስ (ዮሐ. 17፥1) ነፍሱን በፈቃዱ ሰጠ።  ሆኖም ጌታችን በሞቱ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በትንሣኤውም ላይ ሥልጣን ነበረው። ይህም “በትንሣኤው ላይ የመለኮት ባሕርይው ተሳታፊ መሆኑን ያመላክታል።”[24] ማንም ሰው በራሱ ላይ ይህ ዐይነቱ ሥልጣን የለውም! ጌታ ኢየሱስ ግን እርሱ አምላክ ነውና በራሱ ትንሣኤ ላይ ሥልጣን ነበረው! ጌታ ኢየሱስ በዚህ መልኩ መለኮትነቱን ከገለጠ በኋላ፣ ነፍሱን ለመስጠትና ለማንሣት ትእዛዙን (ተልእኮውን) የተቀበለው ከአባቱ መሆኑን ገልጿል፤ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ” በማለት። ስለዚህም መለኮትነቱ እና በአባቱ መታዘዙ በአንድነት የታሰሩ ነገሮች ናቸው። ይህም የጌታ ኢየሱስ ልጅነት መለኮትነት እንደ ሆነ ያጸናል! የዕብራውያን መልእክትም በመጀመሪያ ምዕራፉ የሚያወራው የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት መለኮትነት መሆኑን ነው።

 

በቅዱስ ዮሐንስ ዘገባ መሠረት፣ አይሁድ ጌታችንን ለመግደል የፈለጉባቸው ምክንያቶች ሁለት ናቸው፤ ሰንበትን (እነርሱ የሚያከብሩበትን መንገድ) መሻሩ እና እግዚአብሔርን “የገዛ አባቱ” (“his own Father” - AMP, ASV, ESV, NASB, NRSV, NIV, RSV) አድርጎ ማቅረቡ (ዮሐ. 5፥18)። “የገዛ አባቱ” የሚለው ግሪክኛው “ፓቴር ኢዲዮ(πατέρα ἴδιον) ይለዋል። “ፓቴር” (πατήρ) አባት ማለት ሲሆን፣ “የገዛ/የራሱ/የግሉ” የሚል ትርጓሜን ያዘለው “ኢዲዮስ” (ἴδιος) የሚለው ቃል ደግሞ፣ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ዐይነት ግንኙነት ሌሎች እንደሌላቸውና እርሱ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት ልዩ መሆኑን የሚገልጽ ነው።[25] አይሁድ ሰው ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ቢቀበሉም እንኳ፣ ጌታ ኢየሱስ እግዚአብሔርን “የገዛ አባቱ” አድርጎ ማቅረቡ ያልተዋጠላቸውና ሊገድሉት ያሤሩት ለዚህ ነው፤ የኢየሱስ አነጋገር ራስን ከእግዚአብሔር ጋር ማስተካከል መሆኑን ተረድተዋልና![26] ይህ ደግሞ የአንድ ጊዜ ክሥተት ብቻ አልነበረም (ዮሐ. 10፥31-36፤ ማቴ. 26፥63-66)። ሐዋርያው ጳውሎስም ይህንኑ የግሪክ ቃል (ἴδιου) ተጠቅሞ፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር “የገዛ ልጁ” መሆኑን ይናገራል (ሮሜ 8፥32)። ይህም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ፣ እግዚአብሔርም የኢየሱስ አባት የሆነበት መንገድ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ካለው ልጅነት እና አባትነት ጋር አንድ አለመሆኑን ያስረዳናል!

 

የእግዚአብሔር ልጅነትን ለማሳየት በግሪኩ ጥቅም ላይ ከሚውሉት ቃላት መካከል “ቴክኖን ቴኡ” (τέκνον θεού) በሚሉት ቃላት ኢየሱስ ተጠርቶ አያውቅም።[27] ሐዋርያው ዮሐንስ በተለይ የኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅነት ለማመልከት “ሁዮስ (υιος)” የተሰኘውን የግሪክ ቃል ሲጠቀም፣ የአማኞችን የእግዚአብሔር ልጅነት ለማሳየት ግን “ቴክና (τέκνα)” የሚለውን ቃል ነው የተጠቀመው።[28] እግዚአብሔር ለኢየሱስ ያለው አባትነት እና ለእኛ ያለው አባትነት በፍጹም አንድ ዐይነት አይደለም።[29]

 

ጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “አባታችን ሆይ” በማለት እንዲጸልዩ ቢያስተምርም (ማቴ. 6፥9)፣ እርሱ ግን እግዚአብሔርን ሲጠራ “አባት ሆይ” እና “አባቴ ሆይ” በማለት ነበር (ዮሐ. 20፥17፤ 11፥41)፤ ይህም ከአብ ጋር የተለየ ግንኙነት እንደ ነበረው ያሳያል።[30] ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ እግዚአብሔርን፣ “አባቴ እና አባታችሁ” በማለት ጠራው እንጂ (ዮሐ. 20፥17)፣ ራሱን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በአንድነት አድርጎ “አባታችን” በማለት ጠርቶት አያውቅም። ስለዚህም በዚህ ገጽታው የእኛ ልጅነት ከእርሱ ልጅነት የተለየ ነው።

 

4.1.1  መለኮታዊ  ልጅነቱ  መቼ ጀመረ?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ “[እግዚአብሔር] አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና” ይላል (ሮሜ 8፥29)። በተጨማሪም፣ “[እግዚአብሔር አብ] ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን” ሲል ይናገራል (ኤፌ. 1፥4)። እኛን አማኞችን የመረጠን አብ፣ የተመረጥነውም በወልድ በኩል ሲሆን፣ ምርጫው የተካሄደው “ዓለም ሳይፈጠር” በፊት ነው። ይህ ደግሞ ዓለም ከመፈጠሩም በፊት በሥሉስ አምላክ መካከል የሥራ (የሚና) ክፍፍል መኖሩን ያስተምረናል። በዚህ የሚና ልዩነት መሠረትም እግዚአብሔር ወልድ የእግዚአብሔር አብ ልጅ ነው፤ ይህም በአብና በወልድ መካከል ያለውን ልዩ ግንኙት ያሳያል።

 

አብ አባት ነውና የማቀድና የመምራት ሚና ሲኖረው፣ ወልድ ደግሞ ልጅ ነውና የመታዘዝ ሚና አለው። በባሕርይ እና በመለኮትነት እኩል ቢሆኑም፣ የሥራ ክፍፍል አላቸው። እኛን ለማዳን የተደረገው ውሳኔ ድንገተኛ የሚና ክፍፍል አላመጣም።[31] አብ ፈጣሪ ነው፤ የፈጠረው ግን በወልድ በኩል ነው (ዕብ. 1፥2)። መንፈስ ቅዱስም በፍጥረት ላይ የሥራ ድርሻ ነበረው (ዘፍ. 1፥2፤ ኢዮብ 26፥13)። ሥራውን ማንም ያድርገው ማንም፣ ባለቤትነቱ የሥሉስ አምላክ ነው።

 

በሥሉስ አካላት መካከል የእርስ በርስ ግንኙነት የተጀመረው በታሪክ ውስጥ አንድ ወቅት ላይ አይደለም፤ ለዘላለምም ነበር።[32] አብ እንደ አባት ልጁን የወደደው ዓለም ሳይፈጠር ነው። ጌታ ኢየሱስ፣ “አባት ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ …” ሲል መጸለዩ ይህንን ያረጋግጣል (ዮሐ. 17፥24)።  በአብና በወልድ መካከል መከባበርም የጀመረው ዓለም ሳይፈጠር ነው፤ ስለዚህም ጌታችን፣ “ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ” ሲል ጸልዮአል (ዮሐ. 17፥5)። በመለኮት አካላት መካከል ዘላለማዊ መከባበር ነበር።[33] መላለሙ ከመፈጠሩ በፊት፣ እግዚአብሔር አምላክ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በሚል ልይዩነት እና አንድነት ይኖር ነበርና።

 

አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በመለኮትነት አቻ ቢሆኑም፣ የሚና ልዩነት ከሌላቸው አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር ልይዩነት አይኖራቸውም። ስለዚህ ሦስት አብ፣ ወይም ሦስት ወልድ፣ ወይም ሦስት መንፈስ ቅዱስ የማይሆኑበት ምክንያት የለም። ነገር ግን ከዘላለም እስከ ዘላለም አብ አብ ነው፤ ወልድም ወልድ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ነው። ይህም ከትምህርተ ሥላሴ አዕማድ አንዱ ነው!

 

የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ግንኙነት በጊዜ ውስጥ የተከሠተ ሳይሆን ዘላለማዊ ነው።[34] ከዚህም የተነሣ አብ በአባትነቱ ላኪ፣ ወልድ ደግሞ በልጅነቱ ተላኪ ነው (ዮሐ. 5፥23፤ ገላ. 4፥4፤ 1ዮሐ. 4፥14)። አብ እና ወልድ ላኪ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ተላኪ ነው (ዮሐ. 16፥7፤ 14፥26)። አብ ወልድን ያከብራል (ዮሐ. 17፥5፡24)፤ መንፈስ ቅዱስም ወልድን ያከብራል (ዮሐ. 16፥14)። “ወልድ [በማንነቱ ሳይሆን] በሚናው (በሥራው) ለዘላለም ከአብ የበታች ካልሆነ፣ አብ ለዘላለም ‘አብʼ ሊሆን አይችልም፤ ወልድም ለዘላለም ‘ወልድʼ ሊሆን አይችልም። ይህም ሥላሴ ለዘላለም አልነበረም ማለት ነው።”[35]

 

እግዚአብሔር ወልድ የእግዚአብሔር አብ ልጅ የሆነው ወደ ምድር ሲመጣ አይደለም፤ ቀጣዮቹ ጥቅሶች ይህንን ፈንትወውታል። “እግዚአብሔር … ዓለም በልጁ እንዲድን እንጂ በዓለም እንዲፈርድ ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ. 3፥16-17)፤ “እግዚአብሔር … ልጁን ላከ” (ገላ. 4፥4)፤ “የሚወደው አንድ ልጅ ገና ነበረው፤ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ እርሱን ወደ እነርሱ ላከ” (ማር. 12፥6-8)። “እግዚአብሔር የገዛ ልጁን … ልኮ” (ሮሜ 8፥3)፤ “ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ” (ዕብ. 1፥2)፤ እግዚአብሔር የበኵር ልጁን ወደ ዓለም በላከ ጊዜ” (ዕብ. 1፥6፤ የ1997 ትርጕም)፤ “የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” (1ዮሐ. 3፥9)፤ “እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል። … ልጁን እንደ ላከ … አባትም ልጁን የዓለም መድኀኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን” (1ዮሐ. 4፥9-10፡14)። እግዚአብሔር ወልድ ወደ ምድርም ተልኮ ሲመጣና ሲገለጥም ሆነ ዓለምን ሲፈጥር የእግዚአብሔር ልጅ (ወልደ እግዚአብሔር) ነበር። ልጅነቱ የጀመረበት ቀን፣ ሰዓት፣ ቅጽበት የለም፤ ልጅነቱ ከዘላለምም ነበር!

 

ኢየሱስ በዚህ ረገድ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ሰው ሆኖ ሲወለድ ቢሆን ኖሮ የበኵር ልጅ ባልሆነም ነበር። እስራኤል (ዘፀ. 4፥22) ወይም ኤፍሬም (ኤር. 31፥9)፣ እንዲሁም ዳዊት (መዝ. 89፥27) በኵር ተብለዋል። አዳምም የመጀመሪያው ሰው በመሆኑ እንደ በኵር ሊታሰብ ይችላል።

 

4.1.2  “ያሕዌ” እና “የያሕዌ መልአክ”

ከእግዚአብሔር ወልድ የዘላለም ልጅነት ጋር የሚጣጣሙ ማስረጃዎች በብሉይ ኪዳንም አሉ። ለምሳሌ እግዚአብሔር በሚነድድ ቊጥቋጦ መካከል ለሙሴ የተገለጠበትን መንገድ ማጤን ይቻላል (ዘፀ. 3፥1 - 4፥17)። ታሪኩ ሲጀምር ለሙሴ የተገለጠው አካል፣ “የእግዚአብሔር መልአክ” ተብሎ ነው የተዋወቀው (3፥2)። ከዚያ በኋላ ግን፣ በታሪኩ ውስጥ “የእግዚአብሔር መልአክ” መባሉ ቀርቶ “እግዚአብሔር” እየተባለ ነው የቀረበው (3፥4፡6፡7፤ 4፥2፡4፡5፡6፡10፡11፡14)። ሙሴም የሚያነጋረውን አካል ስም ሲጠይቅ፣ “ያለና የሚኖር” ወይም “ያህዌ (יהוה)” የሚል ምላሽ አግኝቷል (3፥14)። ተናጋሪው አካል፣ “እኔ የአባትህ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ ነኝ” በማለት ራሱን ለሙሴ አስተዋውቋል (3፥6፡15)። በተጨማሪም በንግግሩ ውስጥ ሁሉ፣ “የሕዝቤን ጩኸት ሰማሁ፤ መከራቸውን አየሁ፤ አድናቸዋለሁ፤ ከግብፅ አወጣቸዋለሁ፤ አንተንም እልክሃለሁ፤ ወዘተ.” በማለት የአንደኛ መደብ ቋንቋን ነው የሚጠቀመው። እሳት ከእግዚአብሔር መገለጥ ጋር እንደሚያያዝም ይታወቃል (ዘፀ. 13፥21-22፤ 19፥18፤ 40፥38፤ 1ነገ. 18፥24፡38)። ታዲያ ይህ መልአክ ማነው?   

 

ለያዕቆብ የተገለጠለትም “መልአክ” ራሱን “የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ” በሚል ነው የገለጠው (ዘፍ. 31፥11-13)። በሌላ ስፍራ ደግሞ፣ ኀጢአትን  ይቅር የማለትና ያለ ማለት ሥልጣን ያለው ሆኖ ቀርቧል (ዘፀ. 23፥20-21)። እስራኤላውያንን ከግብፅ ያወጣው እርሱ መሆኑን፣ ከእነርሱም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንደሚጠብቅ፣ እነርሱ ግን የገቡለትን ቃል ባለመጠበቃቸው ማዘኑንም ይናገራል (መሳ. 2፥1-3)። ለጌዴዎን ሲገለጥም (መሳ. 6፥11-24)፣ “የእግዚአብሔር መልአክ” (ቊ. 11፡12፡20፡21) እና “እግዚአብሔር” (ቊ. 14፡16፡20) እየተባለ ተጠርቷል። በዘካርያስ 12፥8ም በዚሁ መልክ ተጠቅሷል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ በዚህ መልኩ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ሆኖ የተገለጠ መልአክ የለም።[36] ለምን?

 

ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት፣ “መልአክ” ከሚለው ቃል ትርጓሜ መጀመር ግድ ይሆናል። መልአክ በዕብራይስጥ ማላክמַלְאָך) ) ሲሆን፣ መልአክ፣ መልእክተኛ፣ ልዑክ የሚሉ ትርጓሜዎችን ይዟል።[37] (የሚገርመው ነገር በግሪኩም ትርጓሜው ይኸው መሆኑ ነው![38]) ለምሳሌ፣ በምሳሌ 17፥11 የሚገኘውን ይህንኑ “ማላክ” የተሰኘ ቃል፣ የ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ “መልአክ” ሲለው፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም እና የ1997 ትርጕም “መልእከተኛ” ብለውታል። በ2ኛ ነገሥት 1፥3 ውስጥ 2 ጊዜ የሚገኘው ይኸው ቃል፣ በዚያው ጥቅስ ውስጥ “መልአክ” እና “መልእክተኞች” ተብሎ ነው የተተረጐመው። በዕብራይስጡ “ማላከ ሞት” (מַלְאָךְ מָוֶת) የሚለው ስያሜ “የሞት መልእክተኛ” (ምሳሌ 16፥14)፣ “ማልአክ ሻሎውም” (מַלְאָךְ שָׁלֹום) ደግሞ “የሰላም መልእክተኞች” (ኢሳ. 33፥7) ተብሏል።[39] ማላክ የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን ውስጥ 213 ጊዜ ሲገኝ፣ ለምሳሌ NIV መጽሐፍ ቅዱስ፣ 108 ጊዜ መልአክ/መላእክት፣ 83 ጊዜ መልእክተኛ/መልእክተኞች፣ 8 ጊዜ ደግሞ ልዑክ/ልዑካን (envoy, delegation, official) በማለት ተርጕሞታል።[40]

 

ስለዚህ ይህ “የቤቴል አምላክ”፣ “የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ” የሆነውና “ያሕዌ ነኝ” ያለው “መልአክ” በእርግጥም ያህዌ መሆኑ እንደማያጠራጥር ሁሉ፣ መልእክተኛ (የተላከ) መሆኑም አያጠራጥርም። ይህ ደግሞ አስቀድመን ካነሣነው ሐሳብ ጋር ይገጥማል። እግዚአብሔር ወልድ፣ የእግዚአብሔር አብ ልጅ የሆነው ከዘላለምም ነውና በብሉይ ኪዳን የአባቱ መልእከተኛ በመሆን (እየተላከ) ይመጣ እንደ ነበር መናገር ይቻላል። እርሱ ያሕዌም፣ የያሕዌ መልእክተኛም ነው። አብ በአባትነቱ ወልድን ይልካል፤ ወልድም በልጅነቱ ለአብ ይላካል! የእግዚአብሔር መልአክ የተሰኘው፣ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ከመምጣቱ በፊት (ቅድመ ትስጉት) የተገለጠበት መገለጫ ማንነቱ ነበር። ከሙሴ በፊት፣ ለአብርሃምም፣ ለአጋርም፣ ለያዕቆብም የተገለጠው ያ እግዚአብሔር ወልድ ነው።

 

ኀይሉ ዮሐንስ፣ ቃል ሥጋ ከመንሣቱ በፊት አባት እንደ ነበር ለማስረዳት ኢሳይያስ 9፥6ን ይጠቅሳል። ሆኖም፣ “ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና … የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” የሚለው ትንቢት፣ ወልድ ቀድሞ አባት ሆኖ ስለ መኖሩ የሚናገር አይደለም። በአንድ በኩል፣ “የዘላለም አባት” ማለት ዘላለማዊ ማለት ነው።[41] በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሚወለደው ሕፃን ለሕዝቡ የሚራራ አባት እንደሚሆን ነው የሚተነብየው። ኢዮብ፣ “ለድኻው አባት ነበርኩ” እንዳለው ሁሉ (29፥16)፣ ኢየሱስም ለሕዝቡ የሚራራና የሚያዝን አባት ይሆናል። መሲሑ በንጉሥነቱ በመልካም በማስተዳደር ሕዝቡን ያሳርፋል (ኢሳ. 22፥21)። የምንባብ ክፍሉ ወደፊት ስለሚፈጸም ክስተት የሚናር ከመሆኑም ባሻገር፣ በጥቅሱ ውስጥ “አባት” የሚለው ቃል በአብና በወልድ መካከል ያለውን ግንኙነት በጭራሽ የሚናገር አይደለም፤ በወልድና በሕዝቡ መካከል የሚኖረውን እንጂ። እግዚአብሔር አብ አባት ነው ስንል ግን፣ በአብና በወልድ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከት ነው። ይህም ግንኙነት ዘላለማዊ ነው!

 

ቤተ ክርስቲያን ይህንን ከጥንትም ተቀብላ ኖራለች። ለምሳሌ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚቀበሉት የኒቅያ የሃይማኖት መግለጫ (በ4ኛው ክፍለ ዘመን)፣ የአትናቴዎስ የእምነት መግለጫ (በ4ኛው እና በ5ኛው ክፍለ ዘመን)፣ የኬልቄዶን የእምነት መግለጫ (በ5ኛው ክፍለ ዘመን) ይህንኑ አጽንተዋል። በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተደነገጉት የሉተራውያኑ “የኦግስቡርግ የእምነት መግለጫ” (The Augsburg Confession)፣ “ትንሹ የክርስትና ትምህርት” (The Small Catechism) እና “ትልቁ የክርስትና ትምህርት” (The Large Catechism) ከዚሁ ይመደባሉ። የ16ኛው ክፍለ ዘመን “የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አንቀጾች (ሠላሳ ዘጠኙ አንቀጾች)” (Articles of Religion (Thirty-Nine Articles) – Church of England)፣ የ17ኛው ክፍለ ዘመን “የዌስትሚኒስተር የእምነት መግለጫ” (Westminster Confession of Faith) እና የ20ኛው ክፍለ ዘመን “የመጥምቃውያን እምነትና መልእክት፤ የደቡብ መጥምቃውያን ጉባኤ” (The Baptist Faith and Message - Southern Baptist Convention) ይህንኑ የክርስቶስ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ልጅነት የሚናገሩ ናቸው። የእግዚአብሔር ወልድን ዘላለማዊ ልጅነት የሚቃረን የቤተ ክርስቲያን የእምነት መግለጫ ከቶውኑ ኖሮ አያውቅም።

 

4.2  የእግዚአብሔር ልጅነት እና ሰው-ነት

እግዚአብሔር በፈጣሪነቱ እና በአምላክነቱ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አባት ነው (ኢሳ. 63፥16፤ 64፥8፤ ሚልክ. 2፥10)። የየትኛውም አባትነት መነሻም እርሱ ነው (ኤፌ. 3፥14-15)። ቃል በመንፈስ ቅዱስ ተኣምራዊ ድርጊት ሰው ሆኖ ከመወለዱ አኳያ እግዚአብሔር አባቱ ነው፤ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ፣ “ከእግዚአብሔር የተወለደው” በማለት ኢየሱስን ይጠራዋል (1ዮሐ. 5፥18)። ምክንያቱም ኢየሱስ በአካላዊ ውልደቱ፣ ከእግዚአብሔር አብ የተላከና በመንፈስ ቅዱስ የተፀነሰ በመሆኑ፣ እንዲሁም ከሙታን በመነሣቱና ወደ ሕይወት በመመለሱ “ከእግዚአብሔር የተወለደ ነው” (ቈላ. 1፥18)። [42]

 

በትልቅ ንጉሥ (ንጉሠ ነገሥት) ሥር ሆነው፣ በእርሱ ሥልጣን የሚያስተዳድሩና ታማኝነታቸውን ለእርሱ ያደረጉ ነገሥታት “ልጅ” ተብለው መጠራታቸው በጥንቱ ቅርብ ምሥራቃዊ ዓለም የተለመደ ነበር።[43] ለምሳሌ፣ እግዚአብሔር ለዳዊት አባት፣ ዳዊትም ለእግዚአብሔር ልጅ ነበር። “ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት። … እርሱ፦ አባቴ አንተ ነህ፥ አምላኬ የመድኀኒቴም መጠጊያ ይላል። እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ” (መዝ. 89፥18-38)። መዝሙር 110ም ከዚሁ የሚመደብ ነው።

 

እግዚአብሔር ለዳዊት ብቻ ሳይሆን፣ ለሰለሞንም አባት እንደሚሆን ተነግሯል። ለምሳሌ ለንጉሡ ዳዊት፣ ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ ከአባቶችህም ጋራ ባንቀላፋህ ጊዜ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፥ መንግሥቱንም አጸናለሁ። እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፤ የመንግሥቱንም ዙፋን ለዘለዓለም አጸናለሁ። እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል …” የሚል ተስፋ ሰጥቶታል (2ሳሙ. 7፥12-15)። ስለዚህም ዳዊት፣ ከልጆቼ ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል። እርሱም፦ ልጅ ይሆነኝ ዘንድ መርጬዋለሁና፥ እኔም አባት እሆነዋለሁና … አለኝ” ሲል ተናገረ (1ዜና 28፥5-7)።

 

ነገሥታቱ የሚነግሡበት ቀን የእግዚአብሔር ልጅነታቸው ጅማሬ ተደርጎ ይወሰዳል። ስለዚህም፣ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ” የሚለው መሲሓዊ ትንቢት፣ መሲሑ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነበት መነሻ፣ “ዛሬ” ተብሎ የሚታወቅ ቀን እንዳለው ያሳስበናል። ይህም ከኢየሱስ መለኮትነት ጋር ሳይሆን፣ ከመሲሕነቱ፣ ከአገልጋይነቱ፣ ሰው ከመሆኑ ጋር ይያያዛል።

 

መሲሑ በሥጋ የዳዊት ዘር በመሆኑ ዙፋን (ንግሥና) የተገባው ነው፤ ስለ መሲሑ የዳዊት ልጅነት በብሉይ ኪዳን በርካታ ትንቢቶች ተነግረዋል (መዝ. 89፥1-4፤ 132፥11፡17፤ ኢሳ. 9፥7፤ 11፥1፤ 16፥5፤ ኤር. 23፥5-6፤ 33፥15-16፤ ሕዝ. 34፥23-24፤ 37፥24-25፤ ዘካ. 3፥8፤ 6፥12)። ጌታችን በሥጋ የዳዊት ዘር መሆኑም እንደዚሁ በአዲሱ ኪዳን ተረጋግጧል (ማቴ. 1፥1፤ ሉቃ. 1፥27፡32፤ 2፥4፡11፤ ሮሜ 1፥3፤ 2ጢሞ. 2፥8፤ ራእይ 22፥16)። በርካቶችም “የዳዊት ልጅ” በማለት ይጠሩት ነበር (ማቴ. 9፥27፤ 15፥22፤ 20፥31፤ 21፥15፤ 22፥42)።

 

“አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ” የሚለው የንግሥና ወግ መሲሑን የሚመለከት መሆኑ የተነገረው በመዝሙር 2 ነው። “የምድር ነገሥታት ተነሡ፥ አለቃዎችም በእግዚአብሔርና በመሲሑ ላይ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ። … እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ። ትእዛዙን እናገራለሁ፤ እግዚአብሔር አለኝ፦ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ። ለምነኝ፥ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ። በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ፥ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃዎች ትቀጠቅጣቸዋለህ” (መዝ. 2፥1-12)። ሐዋርያትም ትንቢቱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያመለክት መስክረዋል (የሐዋ. 4፥24-26)።

 

በዚህም ስለ ዳዊት ዙፋን የተነገረው ትንቢት በኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ ፍጻሜውን አግኝቷል! “አንተ ልጄ ነህ፤ ዛሬ ወልጄሃለሁ” የሚለው ትንቢት ለኢየሱስ ንግሥና (በዳዊት ዘርነቱ በኩል ላለው) የተነገረ ነውና። ምክንያቱም በመለኮትነቱ ለእግዚአብሔር ልጅነቱ መነሻ ቀን፣ ጅማሬ የለውም፤ ከዘላለምም የእግዚአብሔር ልጅ ነው። በሥጋ የዳዊት ዘርነቱ በኩል ያለው የእግዚአብሔር ልጅነቱ ግን መነሻ ቀን አለው፤ ይኸውም ትንሣኤው ነው።

 

ትንሣኤው የንግሥናው ቀን ነው! ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ፣ አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና” ሲል ገልጾታል (የሐዋ. 13፥33)። በተጨማሪም፣ “በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኀይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ” በማለት የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ከትንሣኤው ጋር ያለውን ትሥሥር ያጸናል (ሮሜ 1፥4)። “ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፤ እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኀይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ” እንደ ተባለ (1ጴጥ. 3፥21-22)፣ ኢየሱስ በአብ ቀኝ የተቀመጠው ነግሦ ነው። መንገሡም የእግዚአብሔር ልጅነቱ ነው።

 

በሌላ በኩል ደግሞ የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ከእስራኤላውያን የእግዚአብሔር ልጅነት ጋር ሊያያዝ ይችላል። እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር በገቡት ኪዳን የተነሣ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነው ነበር፤ ይህም ኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር የተለየ ግንኙነት ፈጥሮላቸዋል (ዘዳ. 32፥6፤ ኢሳ. 1፥2፤ 63፥8፡16፤ ሮሜ 9፥4)። ሆኖም እነርሱ ኪዳኑን አልጠበቁም። ስለዚህም ጌታ ኢየሱስ እስራኤልን ወክሎ በመግባት የእስራኤል የእግዚአብሔር ልጅነት በእርሱ ፍጻሜ እንዲያገኝ አድርጓል። ጌታችን በልጅነቱ ወደ ግብፅ መውረዱ፣ ከዚያም ከግብፅ መጠራቱ (ሆሴዕ 11፥1፤ ማቴ. 2፥15)፣ እንዲሁም የዮሐንስን ጥምቀት መጠመቁ ከዚሁ ጋር ይያያዛል። በምድረ በዳ በሰይጣን ተፈትኖ ማለፉም፣ በምድረ በዳ ተፈትና የወደቀችውን እስራኤልን ወክሎ ያደረገው ነው።[44]

 

4.3  የእግዚአብሔር ልጅነታችን ጕዳይ

4.3.1  ልጅነት ሁል ጊዜም የባሕርይ (Essence) አንድነት ማረጋገጫ ነውን?

አባት እና ልጅ በተፈጥሮ ባሕርይ (essence) አንድ መሆናቸው ይጠበቃል። ስለዚህም አባቴ ሰው ነው፤ እኔም ሰው ነኝ፤ ልጆቼም ሰዎች ናቸው። ነገር ግን አባት እና ልጅ የሚሉት ቃላት ሁል ጊዜም ጥቅም ላይ የሚውሉት በዚህ ዐውድ አይደለም።

 

ለምሳሌ፣ መላእክት “የእግዚአብሔር ልጆች” ተብለዋል (ኢዮብ 1፥6፤ 2፥1)። በተጨማሪም መላእክት ቅዱሳን (መዝ. 89፥5፡7)፣ እንዲሁም መናፍስት (ዕብ. 1፥14) ናቸው። “ሰው መንፈስ ነው” ባዮች፣ “ሰው በሥጋ ውስጥ መኖሩ” እሥራት እንደሆነበት ያስተምራሉ። በዚህ አካሄድ፣ መላእክት መንፈስ ብቻ በመሆናቸው (ቊሳዊ አካል ስለሌላቸው) ከእኛ የተሻለ ደረጃ ነው ያላቸው። ግና መላእክት ቅዱሳንም፣ መናፍስትም፣ የእግዚአብሔር ልጆችም ሆነው፣ በጭራሽ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ አይደሉም። ታዲያ እኛ “መንፈስ ነን” ብለን፣ “የእግዚአብሔር ልጆች ነን” ብለን፣ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ መሆናችንን ለማሰብ እንዴት ተቻለን? ሰው አንድ፣ መላእክት ሌላ፣ እግዚአብሔርም ሌላ ናቸው። መንፈስ እና የእግዚአብሔር ልጅ መሆን በራሱ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ወይም እኩል አያደርግምና!

 

በድርጊታቸውና በሚያሳዩት ጠባይ እግዚአብሔርን ወይም ሰይጣንን የሚመስሉ ሰዎችም የእግዚአብሔር ወይም የሰይጣን ልጆች ይባላሉ። ሐሰትን የሚወድዱ (ዮሐ. 8፥44)፣ ተንኮለኞችና የጽድቅ ጠላቶች (የሐዋ. 13፥10)፣ ጽድቅን የማያደርጉና ወንድማቸውን የማይወዱ (1ዮሐ. 3፥10)፣ “የዲያብሎስ ልጆች” ተብለዋል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ከዲያብሎስ ጋር አንድ አካል፣ አንድ አምሳል፣ እንዲሁም የዲያብሎስ ቊራጮች ይሆናሉን? በሌላ በኩል ደግሞ ጠላቶቻቸውን የሚወድዱና መልካም የሚያደርጉ (ሉቃ. 6፥35)፣ የሚያስተራርቁ (ማቴ. 5፥9)፣ ጽድቅን የሚያደርጉ (1ዮሐ. 3፥10) “የእግዚአብሔር ልጆች” ተብለዋል። እነዚህም ቢሆኑ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ አምሳል፣ አንደ አካል ሊሆኑ አይችሉም!

 

4.3.2  አማኞች እና የእግዚአብሔር ልጅነታችን

እግዚአብሔር የፍጥረት ሁሉ ባለቤት፣ አስገኚ እና መጋቢ በመሆኑ ሰው ሁሉ በተፈጥሮው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። “ለሁላችንም አንድ አባት ያለን አይደለንምን? አንድ አምላክ የፈጠረን አይደለንምን?” መባሉ ለዚህ ነው (ሚልክ. 2፥10)። ማንኛችንም የተፈጠርነውና ሕይወትን ያገኘነው በዕድልና በአጋጣሚ አይደለምና።

 

እዚህ ጋ ግን አንድ ነገር መስተዋል አለበት። ከእግዚአብሔር ፈጣሪነት አኳያ ሲታይ፣ ሰው ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም፣ እግዚአብሔርን ከማመን እና ጽድቅን ከመከተል አኳያ ሲታይ ደግሞ፣ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆናቸው ገጽታ ይቀየራል። “እግዚአብሔር አባታችን ነው” ላሉት አይሁድ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “እግዚአብሔር አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ … እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ” በማለት የመለሰላቸው ለዚህ ነው (ዮሐ. 8፥42-44)።

 

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን፣ ሁላችንም ከፍጥረታችን የዐመፅ፣ የቊጣ፣ የጥፋት፣ የዲያብሎስ ልጆች ነበርን። እግዚአብሔርን የማይታዘዙ ልጆች ሆነን (ኤፌ. 2፥2፤ 5፥6)፣ “የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፣ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር የነበርን … የቊጣ ልጆች ነበርን” (ኤፌ. 2፥3)። ስለዚህም “የእግዚአብሔር ልጅነት በተፈጥሮአዊ ልደት ወደዚህ ምድር ለገባ ሁሉ የሚበረከት ሁሉን አቀፍ ሹመት አይደለም፤ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተል የሚቀበለው ልዕለ ተፈጥሮአዊ ስጦታ እንጂ። … የእግዚአብሔር ልጅነትን ያገኘነው ሰው ሆኖ በመወለድ ብቻ ሳይሆን፣ ዳግመኛ በመወለድ ነው።”[45]

 

በመሆኑም፣ ሰው የሌላውን ልጅ (የራሱ ያልሆኑትን ልጆች) የራሱ ልጆች አድርጎ እንደሚወስድ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የዲያብሎስ፣ የዓመፅ፣ የቊጣ ልጆች የነበርነውን እኛን ተቀብሎ የራሱ ልጆች አደረገን፤ የራሱ ልጆች የመሆን ሥልጣንን (መብትን) ሰጠን።[46] እግዚአብሔር ሞትን ድል አድርጎ በተነሣውና በቀኙ በተቀመጠው ልጁ ውስጥ ተቀብሎ የራሱ ልጆች አደረገን። ክርስቶስ ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቶ እንደ ነገሠ ሁሉ፣ እኛም “ብንጸና፣ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን” (2ጢሞ. 2፥12)። “የእግዚአብሔር ልጅ” መሆን ማለትም በኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር መተሳሰር፣ የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ መሆን፣ ለአንድ ተልእኮ በእግዚአብሔር መመረጥ ማለት ነው።

 

እስራኤል የእግዚአብሔር ልጅ ነበረች (ዘፀ. 4፥22፤ ሆሴዕ 11፥1) እስራኤላውያንም እንደ ሕዝብ የእግዚአብሔር ልጆች ነበሩ (ዘዳ. 32፥6፤ ኢሳ. 1፥2፤ 63፥8፤ ሮሜ 9፥4)። ይህም የሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ኪዳን ስለ ገቡ ነው። ኪዳኑም የእግዚአብሔር ወገን፣ የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ፤ የእግዚአብሔር ልዩ ሕዝብ አድርጓቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 9 እንደሚነግረን፣ እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ልጆች ቢሆኑም (ሮሜ 9፥4)፣ በሥጋ እስራኤላዊ ስለ ተኮነ ብቻ የእግዚአብሔር ልጅነትን ማግኘት አክትሟል (ቊ. 6 እና 8)። አሁን አይሁድም ሆኑ አሕዛብ የእግዚአብሔር ልጅነትን የሚያገኙት ክርስቶስን በማመን ብቻ ነው (ቊ. 24-26፤ ገላ. 3፥26)። እስራኤል በኪዳን የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነች ሁሉ፣ አማኞችም በኪዳን ያንኑ ቦታ አግኝተን የእግዚአብሔር ልጆች፣ የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነናል!

 

ልጅነታችንም የሚከተሉት ሂደቶች አሉት።

  • የእግዚአብሔር ልጅነታችን ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በእግዚአብሔር አብ የታቀደ ነው። “ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን” ተብሏልና (ኤፌ. 1፥4)። አብ እንደ ራሱ ልጆች ሊቀበለን፣ የራሱ ልጆች ሊያደርገን አስቀድሞ ነው የደነገገው።
  • በተጨማሪም፣ የእግዚአብሔር ልጆች መደረጋችን የተከናወነው በእግዚአብሔር ወልድ ነው።“በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን …” (ኤፌ. 1፥5)፤ “እግዚአብሔር የወሰነው ጊዜ ሲደርስ፣ ልጁን ልኮ የአይሁድ ወገን ከምትሆን ሴት እንዲወለድ አደረገ። እርሱም፣ በሕግ ዘመን ተወልዶ ከሕግ የባርነት ቀንበር ነጻ በማውጣት፣ የእግዚአብሔር ልጆች አደረገን” (ገላ. 4፥4-5 - ሕያው ቃል)። የእግዚአብሔር ልጆች የተደረግነው በችሎታችንና በብቃታችን አይደለም፤ ያለ ክርስቶስ ቤዝዎት የእግዚአብሔር ልጆች ባልሆንን ነበር!
  • የእግዚአብሔር ልጅነትን ማግኘታችን ተግባራዊ የተደረገው በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው። “ስለዚህ ‘አባ! አባታችን ሆይ!ʼ ብላችሁ የምትጠሩበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ በፍርሃት ለመኖር እንደገና የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁም። የእግዚአብሔር መንፈስ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ይመሰክራል” ተብሏል (ሮሜ 8፥15-16፤ የ1997 ትርጕም)።
  • የእግዚአብሔር ልጅነታችን ፍጻሜ የሚያገኘው በሚመጣው ታላቅ ቀን ነው። “የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና” (ሮሜ 8፥19)።


ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅነታችን በአብ የታቀደ፣ በወልድ የተከናወነ፣ በመንፈስ ቅዱስ ተግባራዊ የተደረገና በሚመጣው ታላቅ ቀን የሚገለጥ ነው። “እኛ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፤ ወደ ፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። እርሱ በሚገለጥበት ጊዜ እናየዋለንና፣ እርሱን እንደምንመስል እናውቃለን” (1ዮሐ. 3፥3፤ አ.መ.ት)።

 

4.4  ልጅነት ሲነጻጸር

ኢየሱስ የዳዊት ልጅ፣ የዳዊት ዘር መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከዚህም ይልቃል። ኢየሱስ ለዳዊት ጌታ ነው (ማቴ. 22፥43-45)። ኢየሱስ ለእኛ ወንድማችን መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን ይህ ሙሉ እውነት አይደለም። እኛ ባሪያዎቹ ነን (ማቴ. 10፥24፤ ሮሜ 1፥1፤ 1ቆሮ. 7፥22፤ ገላ. 1፥10፤ ኤፌ. 6፥6፤ ፊልጵ. 1፥1፤ ቈላ. 4፥12፤ 2ጢሞ. 2፥24፤ ያዕ. 1፥1፤ 2ጴጥ. 1፥1፤ ይሁዳ 1፤ ራእይ 1፥1)። ኢየሱስ ታላቅ ወንድማችን ብቻ ሳይሆን፣ ጌታችንም ነውና እንደ ቶማስ “ጌታዬ አምላኬ” ማለት አለብን (ዮሐ. 20፥28)። ኢየሱስ የሁሉ ጌታ በመሆኑ (የሐዋ. 10፥36፣ ፊልጵ. 2፥11)፣ “ሐዋርያው ጳውሎስ 184 ጊዜ ኢየሱስን ጌታ በማለት ጠርቶታል።”[47] የእግዚአብሔር ልጆች ብንሆንም፣ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ጌታችንና አምላካችን፣ እኛም ባሪያዎቹ ነን። የእኛና የእርሱ የእግዚአብሔር ልጅነት አቻ አይደለም!

  1. ማጠቃለያ

በእግዚአብሔር መልክና አምሳል መፈጠራችንን፣ የእግዚአብሔር ባሕርይ ተካፋዮች መሆናችንን እና የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም ያስተምራል። ዳሩ ግን ከእነዚህ ሦስት ግዙፋን ርእሰ ጕዳዮች መካከል፣ ከእግዚአብሔር ጋር አንዳችም ልዩነት እንደሌለንና እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ እንደምንመስል፣ የእግዚአብሔርን ባሕርያት ሙሉ በሙሉ መውረሳችንንም ሆነ ጨርሰን መካፈላችንን መጽሐፍ ቅዱስ አያረጋግጥም፤ እንዲያውም ተቃራኒውን ነው የሚያስተምረው። ኢየሱስንም መምሰላችን የሚገለጠው እርሱ በሚገለጥ ቀን ብቻ ነው፤ እስከዚያው ግን፣ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሳችንን እያነጻን እንድንኖር ታዝዘናል (1ዮሐ. 3፥2-3)።

 

ሐዋርያው ዮሐንስ እንዳለው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ብንሆንም፣ ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም (1ዮሐ. 3፥2)። ምክንያቱም ኀጢአት የሌለበት ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ የከበረውን ሥጋ ለብሶ፣ ሕመም፣ እርጅናና ሞት ፈጽሞ የማይነካው ሆኖ በተገለጠበት መልክ የተገለጠ ሌላ ሰው በምድር ስለሌለ ነው። ከትንሣኤ በኋላ ግን አማኞች ሁላችን የከበረውን ሥጋ እንለብሳለን (ፊልጵ. 3፥20-21፤ 1ቆሮ. 15፥49)። ከዚያም በሚመጣው ዘላለም፣ በግብረ ገብ ረገድ ኀጢአት አልባ፣ በዕውቀት ረገድ ስሕተት አልባ፣ በአካላዊ ጕዳይም ድካምና ጕድለት አልባ በመሆን ለዘላለም እንኖራለን። እርሱን እንመስላለን ማለት ግን እርሱን እንሆናለን ማለት አይደለምና መቼም እንደ ክርስቶስ ሁሉን ዐዋቂና ሁሉን ቻይ አንሆንም። ምክንያቱም እርሱ ሰው ብቻ ሳይሆን አምላክም ነውና![48] ስለዚህም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች ካሉ ፍጥረታት ጋር በኢየሱስ ስም ተንበርክከን፣ የኢየሱስን ጌትነት እየመሰከርን፣ ለበጉ ለኢየሱስ እና ለእግዚአብሔር እንሰግዳለን (ፊልጵ. 2፥10-11፤ ራእይ 5፥13)። እናመልካለን!

 

ማስታወሻ

  1. ይህ ጽሑፍ እንከኖቹ ተወግደውለት፣ በሁለት እግሮቹ በርትቶ እንዲቆም፣ የወንድም አማረ መስፍን፣ የወንድም ዘላለም መንግሥቱ እና የዶ/ር ተስፋዬ ሮበሌ እገዛ እጅግ አስፈላጊ ነበር። ይህም ሆኖ ግን በጽሑፉ ውስጥ ምንም ዐይነት ስሕተት ቢገኝ፣ ወቀሳው የሚመለከተው እኔን (ጸሓፊውን) ብቻ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል!
  2. ይህን አባባል ቅዱስ ጳውሎስ የወሰደው ከቀርጤሱ ባለቅኔ ኤፒመናይድስ (ቲቶ 1፥12 ላይም ይጠቅሰዋል) ነው። John F. Walvoord; Roy B. Zuck, The Bible Knowledge Commentary: An Exposition of the Scriptures (Wheaton: Victor Books, 1983-c1985), 403.
  3. Marcus Jastrow, Dictionary of the Targumim, the Talmud Babli and Yerushalmi, and the Midrashic Literature (Peabody: Hendrickson, 2006), 1284; Francis Brown, Samuel Rolles Driver and Charles Augustus Briggs, Enhanced Brown-Driver-Briggs Hebrew and English Lexicon, electronic ed. (Oak Harbor: Logos Research Systems, 2000), 853.
  4. Brown et al, Hebrew and English Lexicon, 853.
  5. James Swanson, Dictionary of Biblical Languages with Semantic Domains: Hebrew (Old Testament), electronic ed. (Oak Harbor: Logos Research Systems, Inc., 1997), DBLH 7512, #3.
  6. Warren Baker, The Complete Word Study Dictionary: Old Testament (Chattanooga: AMG Publishers, 2003, c2002), 241.
  7. ዝኒ ከማሁ።
  8. ዌይን ግሩደም (ትርጕም)፤ ስልታዊ ነገረ መለኮት፤ ቅጽ 1፤ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መግቢያ (አዲስ አበባ፤ ኤስ አይ ኤም፤ 2003) ገጽ 501።
  9. ዝኒ ከማሁ፤ 505-06።
  10. የዚህ ሁሉ መነሻው እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑ ነው። ፍቅር ተፈቃሪን እና አፍቃሪን ይሻልና ከአንድ በላይ አካላት ከሌሉ ፍቅር የለም። የእግዚአብሔር ፍቅርነት የሚጀምረው ግን፣ ሰውንም ሆነ ሌሎቹን ፍጥረታት ካስገኘ በኋላ አይደለም። እርሱ ሁሌም ፍቅር ነው። ለፍቅርነቱ ጅማሬ የለውም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ሥሉስ አምላክ ነው። በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ፍቅር (ማር. 1፥11፤ ማቴ. 17፥5)፣ አንድነት (ዮሐ. 17፥11፡22) እና መከባበር (ዮሐ. 17፥5፡24፤ 16፥14) መኖሩ በቅዱሱ መጽሐፍ ተነግሯል። እግዚአብሔርን ፍቅር ያሰኘውም ይሄ በራሱ በእግዚአብሔር አካላት (Godhead) መካከል ያለው እውነተኛ ፍቅር ነው፤ የተፈጠርነውም በዚህ ምሳሌ ነው!
  11. ግሩደም፤ ስልታዊ ነገረ መለኮት፤ 1፡499።
  12. Berkhof, Systematic Theology (Grand Rapids: Eerdmans, 1979), 202.
  13. ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 204።
  14. ከውድቀት ጀምሮ ግን ሰው “መልካሙንና ክፉውን ዐወቀ”። ስለዚህም፣ “ይህ ነገር መልካም ነው፤ ይህኛው ደግሞ ክፉ ነው” በማለት በራሱ ውሳኔ፣ በአብላጫ ድምፅ፣ በብዙሃን ስምምነት ይወስን ጀመር። ከዚህም የተነሣ፣ እግዚአብሔር “ክፉ ነው” ያለውን፣ ሰው “መልካም ነው”፣ እግዚአብሔር “መልካም ነው” ያለውን ደግሞ “ክፉ ነው” የማለት “ነጻነቱን” አስከበረ።
  15. Spiros Zodhiates, The Complete Word Study Dictionary: New Testament, electronic ed. (Chattanooga: AMG Publishers, 2000, c1992, c1993), G2844; Horst Robert Balz and Gerhard Schneider, Exegetical Dictionary of the New Testament, Translation of: Exegetisches Worterbuch zum Neuen Testament (Grand Rapids: Eerdmans, 1990-c1993), 2:303-305.
  16. Zodhiates, Complete Word Study Dictionary, G3444.
  17. ስለ ተወራሲ እና ኢተወራሲ የእግዚአብሔር ባሕርያት በዝርዝር መረዳት የሚፈልጉ አማኞች፣ የዌይን ግሩደምን “ስልታዊ ነገረ መለኮት፤ ቅጽ 1” ገጽ 164-243 ቢያነብቡ ጥሩ መረዳት ያገኛሉ።
  18. በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ቲዎሲስ (theosis) የተሰኘ ግንዛቤ ቢኖርም፣ የእግዚአብሔርን ባሕርያዊ መገለጫዎች ከመካፈል ጋር እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ማንነት ወይም ኑባሬ ሙሉ በሙሉ ከመውሰድ ጋር የተገናኘ አይደለም።
  19. Berkhof, Systematic Theology,
  20. Walter Bauer, A Greek–English Lexicon of the New Testament and Other Early Christian Literature, 3rd ed. (BDAG), revised and edited by Frederick  Danker (Chicago: University of Chicago Press, 2001), S. 658; James Hope Moulton and G. Milligan, The Vocabulary of the Greek Testament (Peabody: Hendrickson, 1930), 416-17; B. M. Newman and Eugene A. Nida, A Translator’s Handbook on the Gospel of John (New York: United Bible Societies, 1980), 24.
  21. Zodhiates, Word Study Dictionary, G3439.
  22. Sutcliffe, The Trinity Hurdle: Engaging Christadelphians, Arians, and Unitarians with the Gospel of the Triune God (Eugene: Wipf and Stock Publishers, 2016), 81.
  23. Bauer et al, Greek–English Lexicon (BDAG), 882.
  24. ESV Study Bible, 2044 (note).
  25. Gerhard Kittel, Geoffrey William Bromiley, Gerhard Friedrich, Theological Dictionary of the New Testament (Grand Rapids: Eerdmans, 1964-c1976), 740.
  26. ESV Study Bible (Wheaton: Crossway Bibles, 2007), 2031 (note); NIV Study Bible (Grand Rapids: Zondervan, 2002), 1637 (note).
  27. Zodhiates, Word Study Dictionary, S. G3439.
  28. H. Marshall, A. R. Millard, J. I. Packer & D. J. Wiseman, New Bible Dictionary, 3rd edition (Nottingham: IVP, 2010), 1123.
  29. Zodhiates, Word Study Dictionary, S. G3439.
  30. Berkhof, Systematic Theology, 91-2.
  31. ESV Study Bible, 2262 (note); ግሩደም፤ ስልታዊ ነገረ መለኮት፤ 1:273።
  32. ESV Study Bible, 2060 (note).
  33. ዝኒ ከማሁ, 2058 (note).
  34. ግሩደም፤ ስልታዊ ነገረ መለኮት፤ 1፡272።
  35. ዝኒ ከማሁ፤ 274።
  36. Marshall, Millard, Packer & Wiseman, New Bible Dictionary,
  37. Swanson, Dictionary of Biblical Languages, DBLH 4855 #1.
  38. መልአክ በግሪኩ “አንጌሎስ (ἄγγελος)” ሲሆን፣ ትርጓሜውም ልዑክ፣ የተላከ፣ መልእክተኛ፣ መልአክ ማለት ነው። (Bauer et al, Greek–English Lexicon (BDAG), 8.) ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በብዙ ስፍራዎች “መልአክ” ተብሎ ቢተረጐምም፣ በማቴዎስ 11፥10፤ በማርቆስ 1፥2 በሉቃስ 7፥24፡27፤ 9፥52፤ በ2ኛ ቆሮንቶስ 12፥7 እና በያዕቆብ 2፥25 መልእክተኛ ተብሎ ነው የተተረጐመው።
  39. ዝኒ ከማሁ።
  40. ቀሪዎቹ ደግሞ ሰዎች፣ ሰላዮች፣ እርሱ፣ እነርሱ … በሚል ተተርጕመዋል። Edward W. Goodrick, John R. Kohlenberger III, The Strongest NIV Exhaustive Concordance (Grand Rapids: Zonderavn, 1999), DBLH 4855.
  41. “በብሉይ ኪዳንም ሆነ በዕብራውያንና በዐረቡ ባህል፣ ‘አባት’ ወይም በዕብራይስጡ ቋንቋ፣ ‘አብ’ የሚለው በተጸውዖ ስምነት ካገለገለ የቃሉ ባለቤት (ቃሉ የተሰጠው ሰው) የተሰጠውን ስም የሚወክል ባሕርይ አለው ማለት ነው። ለምሳሌ፡- ‘አቢዓልቦን’ (2ሳሙ. 23፥31) የሚለው ድርብ ስም፣ ‘አቢ’ ማለትም አባት ከሚለውና ‘ዓልቦን’ ማለት ደግሞ ጠንካራ ከሚሉት ቃላት የተዋቀረ ሲሆን፣ በተገናኝ ሲነበብ (አጫፍረን ስናነበው)፣ ‘የጥንካሬ አባት’ ወይም ‘ጠንካራ’ ማለት ነው። ‘አቢያሳፍ’ (ዘፀ. 6፥24) ማለት፣ ‘የመሰብሰብ አባት’ ወይም ‘ሰብሳቢ’ ማለት ነው። ‘አቢጋኤል’ [አቢግያ] (1ዜና 2፥16) ማለት፣ ‘ከፍ የማለት አባት’ ወይም ‘ከፍ ያለ’ ማለት ነው። አቢጋኤል የሚለው ስም የተሰጠው ለሴት መሆኑን ልብ ይሏል (አባት ነች ማለት ሳይሆን ከፍ ያለች ነች ማለት ብቻ ነው)። በኢሳይያስ 9፥6 ላይ፣ ያለው ‘አቢአድ’ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል፣ ‘የዘላለም አባት’ ወይም ዘላለማዊ ማለት [ነው]”። (ተስፋዬ ሮበሌ፤ ዐበይት መናፍቃን (አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤ/ክ የሥነ ጽሑፍ አገልግሎት፤ 2001) ገጽ 144-45።) በአዲስ ኪዳንም ሰይጣን የውሸት አባት ተብሎ መጠራቱን ያስታውሷል (ዮሐ. 8፥44)።
  42. ESV Study Bible, 2437 (note).
  43. Adela Yarbro Collins, John Joseph Collins, King and Messiah as Son of God: Divine, Human, and Angelic Messianic Figures in Biblical and Related Literature (Grand Rapids: Eerdmans, 2008), 1-24; Marshall et al, New Bible Dictionary, 1122; NIV Study Bible, 789 (note).
  44. Marshall et al, New Bible Dictionary,
  45. I. Packer, Knowing God (Downers Grove፡ IVP, 1973), 200-201.
  46. ልጅ የተደረግንበትን ሁኔታ ለማብራራት ቅዱስ ጳውሎስ “ጉዲፈቻ” (ማደጎ) የሚል ትርጓሜ ያለውን ሂዮቴስያ (υιοθεσια)” የተሰኘ ቃል ለ5 ጊዜአት ያህል ሲጠቀም (ሮሜ 8፥15:23፤ 9፥4፤ ገላ. 4፥5 እና ኤፌ. 1፥5)፣ ሌሎቹ ደግሞ በውልደት ይመስሉታል (ዮሐ. 1፥13፤ 3፥6፤ 1ጴጥ. 1፥23)።
  47. Donald Macleod, The Person of Christ: Contours of Christian Theology (Downers Grove: IVP, 1998), 86.
  48. ESV Study Bible, 2433 (note).

 

 

Read 22201 times Last modified on Tuesday, 09 August 2016 09:47
Paulos Fekadu

ጳውሎስ ፈቃዱ ባለ ትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን፣ በሞያው መምህር ነው። በነገረ መለኮት እና በኮምፒውተር ሳይንስ፣ ከኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት (EGST) እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማስተርስ ዲግሪዎች ያሉት ጳውሎስ፣ እግዚአብሔርን በአእምሮውም ለመውደድ የሚሻ አማኝ ተደርጎ ቢወሰድ ይመርጣል።

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 150 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.