ጉባኤ ለመካፈል ወይም ለአገልግሎት በዕለተ ሰንበት ወደ መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ፕሮግራም ጎራ የሚል ሰው፣ ምእመናኑ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙትን “የሐዋርያት የእምነት መግለጫ” ያደምጣል። የእምነት መግለጫው ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚናገረው አንቀጽ ላይ፣ “በተሰቀለ፣ በሞተ፣ በተቀበረ፣ ወደ ሲኦል በወረደ …” የሚሉ ቃላትን ይዟል።ሌሎች ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትም ይህንኑ ይቀበላሉ፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ጌታ ኢየሱስ ወደ ሲኦል መውረዱን ብቻ ሳይሆን፣ በዚያ ለሚገኙት ነፍሳት ወንጌል መስበኩን የሚናገሩ አማኞችም አሉ።
ከዚህም በከፋ ሁኔታ፣ ጌታ ኢየሱስ ለኀጢአታችን በመስቀል ላይ መሞቱ በቂ ስላልነበረ ወደ ሲኦል ወርዶ በዚያ ተጨማሪ መከራ መቀበሉንና የዘላለም ሞት መሞቱን፣ ከዚያም እዚያው ሲኦል ውስጥ ዳግመኛ መወለዱን እስከ መናገር የሚደፍሩ የኑፋቄ አስተማሪዎችም እየገጠሙን ነው።[1]
ሲኦል የሚለው ቃል በዕብራይስጡ “መቃብር” ወይም “መሞት” የሚል ትርጓሜ አለው (ዘፍ. 37፥35፤ 42፥38፤ 44፥29፡31፤ ዘኁ. 16፥30፤ 1ሳሙ. 2፥6፤ 1ነገ. 2፥6፡9፤ ኢዮብ 14፥13፤ 17፥13፡16፤ 21፥13፤ መዝ. 6፥5፤ 88፥3፤ መክ. 9፥10)።[2] ያዕቆብ፣ “ሽበቴን … ወደ መቃብር [ሲኦል] ታወርዱታላችሁ” (ዘፍ. 42፥38 - አ.መ.ት.) ማለቱ፣ ንጉሥ ዳዊትም፣ “ሽበቱ በሰላም ወደ መቃብር [ሲኦል] እንዲወርድ አታድርግ” እና “ሽበቱን በደም ወደ መቃብር [ሲኦል] አውርድ” ብሎ ልጁ ሰሎሞንን መምከሩ፣ ሲኦል የሰዎች አካል (ሥጋ) የሚሄድበት አካላዊ ቦታ (ማለትም መቃብር) መሆኑን ያስረዳናል፤ ሽበት አካላዊ ነውና!
በተጨማሪም፣ ሲኦልን ሰዎች ሁሉ (አማኞችም አላማኞችም) ሲሞቱ በአካለ ነፍስ የሚከማቹበት ቦታ አድርጎ መውሰድ የተለመደ ምልከታ ነው (መዝ. 89፥48)። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሲኦል ኀጥአን ሲሞቱ ለቅጣት እና ለሥቃይ የሚወርዱበት ቦታ መሆኑ በብዙ አማኞች ዘንድ ግንዛቤ ተይዟል፤ መዝሙር 9፥17፤ 49፥14፤ ምሳሌ 15፥24 እና ሉቃስ 16፥23 የዚህ ምልከታ መነሻ ጥቅሶች ሳይሆኑ አይቀሩም።
ስለዚህ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የጌታ ኢየሱስን ወደ ሲኦል መውረድ ስናነሣ፣ ከመጀመሪያው ትርጕም ጋር አያይዘን አይደለም። ምክንያቱም “መቃብር” ወይም “መሞት” የሚለውን የሲኦል ትርጓሜ ከወሰድን፣ ጌታችን በመስቀል ላይ መሞቱንም ሆነ ከሞቱ በኋላ በመቃብር ማደሩን ቅዱሳት መጻሕፍት በተደጋጋሚ የሚያትቱት ሐሳብ በመሆኑ ነው። ነገር ግን ሲኦል፣ ኀጥአን ለቅጣት የሚወርዱበት ወይም የሞቱ ሰዎች ሁሉ በአካለ ነፍሳቸው የሚከማቹበት ቦታ አድርጎ ከሚወስደው እሳቤ ጋር አያይዘን የጌታችንን ወደ ሲኦል መውረድ አለመውረድ በዚህ ጽሑፍ እንመረምራለን።
እነዚህን ሁሉ ሐሳቦች በቅጡ ከመፈተሻችን በፊት ጌታ ኢየሱስ በሞተበት ቅጽበት ምን እንደ ተከሰተ የወንጌላውያኑን የማቴዎስን፣ የማርቆስን፣ የሉቃስን እና የዮሐንስን ምስክርነት መመልከት ይኖርብናል።
1. የጌታ ኢየሱስ አሟሟት
- “ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ።” (ማቴ. 27፥50)
- “ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ነፍሱንም ሰጠ።” (ማር. 15፥37)
- “ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፦ አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ።” (ሉቃ. 23፥46)
- “ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ፦ ተፈጸመ አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።” (ዮሐ. 19፥30)
አራቱም ወንጌላት የሚነግሩን፣ ጌታ ኢየሱስ ሲሞት ነፍሱን መተዉን ወይም ነፍሱን መስጠቱን ነው። ነፍሱንም የሰጠው ለአባቱ እንደ ሆነ ወንጌላዊው ሉቃስ ግልጽ ያደርገዋል። በመሆኑም ጌታችን ሲሞት ነፍሱ የሄደችው፣ በዐደራ ወደ ተሰጠው እግዚአብሔር አብ ነው። ስለዚህ ጌታ ሲሞት ነፍሱ ወደ ሲኦል አልሄደችም ለማለት የሚያስችል መሠረት አለን።
ምንም እንኳ የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱሳችን (የ1954ቱ እትም) በአራቱም ስፍራዎች “ነፍስ” እያለ ቢጽፍልንም፣ አዲስ ኪዳን የተጻፈበት ወርጅናሌ ቋንቋ የማቴዎሱም፣ የሉቃሱም ሆነ የዮሐንሱ ዘገባ፣ ጌታ ኢየሱስ መንፈሱን መስጠቱን ነው የሚናገረው።[3] የማርቆስ ወንጌል ደግሞ ጭራሹኑ ነፍስም ሆነ መንፈስ የሚልን ቃል አይጠቀምም፤ በታላቅ ድምፅ ጮኾ መሞቱን ብቻ ነው የሚገልጸው። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ሲሞት መንፈሱን (ወይም ነፍሱን) ለአባቱ መስጠቱ፣ ሥጋው ግን በመቃብር ውስጥ የነበረ መሆኑ ሊያስማማን ይገባል።
ሰው ሲሞት፣ ሥጋው ወደ ዐፈር፣ ነፍሱ (መንፈሱ) ደግሞ ወደ እግዚአብሔር የምትሄድ (የሚሄዱ) መሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ነው። ለምሳሌ እስጢፋኖስ በሚሞትበት ጊዜ፣ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል” በማለት ጸልዮአል (የሐዋ. 7፥59)። የሚገርመው፣ እዚህም ጋ ግሪክኛው “መንፈሴን ተቀበል” ማለቱን የሚናገር መሆኑ ነው።[4] በተጨማሪም፣ “በእጅህ ነፍሴን እሰጣለሁ፤ የእውነት አምላክ አቤቱ ተቤዥተኸኛል።” (መዝ. 31፥5)፤ “ዐፈርም ወደነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን ዐስብ።” (መክ. 12፥7)፤ “ስለዚህ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ፥ መልካምን እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ ዐደራ ይስጡ።” (1ጴጥ. 4፥19) የሚሉት ጥቅሶች፣ ሰው ሲሞት መንፈሱ (ነፍሱ) ወደ እግዚአብሔር የመሄዱን ሐሳብ ያጠናክራሉ።
በእርግጥ ጌታችን ሲሞት መንፈሱን (ነፍሱን) ለእግዚአብሔር በዐደራ መስጠቱን፣ እስከ ትንሣዔውም በዚያ መቈየቱን ለመናገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አለን። ይህ ደግሞ በሉቃስ ወንጌል እንደ ተጠቀሰው በጌታ አጠገብ ከተሰቀሉት ወንበዴዎች አንዱ ጌታ በመንግሥቱ እንዲያስበው ሲጠይቅ፣ “እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋራ በገነት ትሆናለህ” በማለት ጌታ ኢየሱስ ከሰጠው መልስ ጋር የሚስማማ ነው (ሉቃ. 23፥43)። ጌታ ኢየሱስ ሰዋዊ መንፈሱን ለእግዚአብሔር ከሰጠ፣ ከዚህ ሰው ጋር በአንድነት ሊሆኑ ይችላሉ ማለት ነው። ጌታ በአካለ ነፍሱ (በመንፈሱ) ሲኦል ከወረደ ግን፣ ከዚህ ሰው ጋር በዚያው ቀን በገነት እንዴት ሊገኝ ይችላል?
አንዳንድ ሰዎች ሲኦልንና ገነትን ፎቅ እና ምድር ቤት አድርገው፣ ገነትንና መንግሥተ ሰማያትን ደግሞ ለያይተው እንደሚወስዷቸው ይታወቃል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ግን የላቸውም። ለምሳሌ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እስከ ሦስተኛ ሰማይ” መነጠቁን ይናገርና ወዲያው ደግሞ፣ የተነጠቀው ወደ ገነት መሆኑን ይነግረናል (2ቆሮ. 12፥2-4)። ስለዚህ ለሐዋርያው ጳውሎስ ሦስተኛ ሰማይና ገነት አንድ መሆናቸውን መናገር ይቻላል።
በተጨማሪም ጌታ ኢየሱስ፣ “ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ” በማለት መናገሩን ከራእየ ዮሐንስ እንነብባለን (2፥7)፤ ስለዚህ የሕይወት ዛፍ የሚገኘው በገነት ነው ማለት ነው። በዚሁ የራእይ መጽሐፍ ምዕራፍ 21 ደግሞ ከሰማይ ስለምትወርደው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ያስረዳል፤ ከዚያም በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አደባባይ መካከል የሕይወት ዛፍ መገኘቱን ይነግረናል (22፥2 እና 14)። የሕይወት ዛፍ በገነት እና በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም መገኘቱ ከተነገረን፣ ሁለቱ ቦታዎች አንድ መሆን አለባቸው። ስለዚህ የሦስተኛ ሰማይ፣ የገነት፣ የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አንድነት አዲስ ኪዳናዊ ድጋፍ አለው ማለት ነው።
ይህ ከሆነ ደግሞ ጌታችን ሲሞት መንፈሱን (ወይም ነፍሱን) ለእግዚአብሔር በዐደራ መስጠቱም ሆነ ንስሓ የገባው ወንበዴ በዚያው ቀን አብሮት በገነት እንደሚሆን ቃል መግባቱ ልዩነት የላቸውም። ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ በአካለ ነፍስ የሄደበት የእግዚአብሔር መኖሪያ እና ገነት የተለያዩ ቦታዎች አይደሉም። ከዚህ አንጻር ሲኦልና ገነትን ማጎራበትም አይቻልም፤ ይህን ለማድረግ ሲኦልንም ወደ ሦስተኛ ሰማይ መውሰድ ይኖርብናል። ገነትና ሦስተኛ ሰማይ አንድ ናቸውና!
ጌታ ኢየሱስ በዚያው ቀን በገነት መገኘቱን መጽሐፍ ቅዱስ ከነገረን፣ ሲኦል መውረዱን እንዴት ልናምን እንችላለን?
2. ጌታ ወደ ሲኦል ለመውረዱ የሚጠቀሱ ጥቅሶች
ጌታ ኢየሱስ ወደ ሲኦል መውረዱ በዋነኛነት ከመጽሐፍ ቅዱስ የመነጨ አስተምህሮ ባይሆንም፣ እነዚሁ ወገኖች ለአቋማቸው በማስረጃነት የሚጠቅሷቸው አንዳንድ ጥቅሶች እንዳሉ ይታያል። ከዚህ ቀጥለን ጥቅሶቹን በየተራ በማውጣት ትክክለኛ ትርጕማቸው ምን እንደ ሆነ ለመቃኘት እንሞክራለን።
- “ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም።” (የሐዋ. 2፥27)
ቅዱስ ጴጥሮስ የዳዊትን ትንቢት ጠቅሶ ይህን ለሕዝቡ የተናገረው ለምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ከተመለሰ፣ የጥቅሱን ዐቢይ ሐሳብ መረዳት አይቸግርም። የጴጥሮስ ስብከት፣ “ዳዊት ከላይ የተጠቀሰውን ትንቢት ቢናገርም፣ እርሱ ግን ሞቶ ቀርቷል፤ መቃብሩም በመካከላችን ይገኛል” በሚል ጀምሮ (ቍ. 29)፣ “ክርስቶስ ግን ሞቶ አልቀረም” በሚል የሚቋጭ መልእክት ያለው ነው (ቍ. 32)። በምንባቡ የምናገኘው “ሲኦል” የሚል ቃልም “መቃብር” ለሚለው ሐሳብ ቅርበት አለው። ዐውደ ንባቡ ከቶውኑም ጌታ ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ወደ ሲኦል መውረዱን የሚናገር አይደለም።
- “ከእምነት የሆነ ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፦ በልብህ፦ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ወይም፦ በልብህ፦ ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው።” (ሮሜ 10፥6-7)
ጥቅሱ ከሙሴ የተወሰደ ይመስላል። “እኔ ዛሬ የማዝህ ይህች ትእዛዝ ከባድ አይደለችም፥ ከአንተም የራቀች አይደለችም። ሰምተን እናደርጋት ዘንድ ስለ እኛ ወደ ሰማይ ወጥቶ እርሷን የሚያመጣልን ማን ነው? እንዳትል በሰማይ አይደለችም። ሰምተን እናደርጋት ዘንድ ስለ እኛ ባሕሩን ተሻግሮ እርሷን የሚያመጣልን ማን ነው? እንዳትል ከባሕሩ ማዶ አይደለችም። ነገር ግን፥ ታደርገው ዘንድ ቃሉ በአፍህና በልብህ ውስጥ ለአንተ እጅግ ቅርብ ነው።” (ዘዳ. 30፥11-14)
በሁለቱ ጥቅሶች መካከል ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ከተረዳን ደግሞ የሐዋርያው ጳውሎስን የአገላለጽ ጭብጥ መረዳት አይከብደንም። ጌታን ከሰማይ ማን ወደ እኛ ያወርድልናል? ከጥልቁስ ማን ወደ እኛ ያቀርብልናል? አይባልም። ጌታ ቅርብ ነው! በመሆኑም ጽድቅ የሚገኘው በእምነት ነው፤ ክርስቶስን ከሰማይ የማውረድን ወይም ከሙታን መካከል የማውጣትን ጀግንነት አይጠይቅም።[5] እግዚአብሔር ክርስቶስን ወደ ምድር ልኮታል፤ ከሙታንም አስነሥቶታል። ስለዚህ እግዚአብሔር ከሰዎች የሚጠብቀው ልዕለ ሰዋዊ ተግባርን ሳይሆን፣ በወንጌሉ ማመንን ነው።[6] እንደ እውነተ ከሆነ፣ ጌታ ከሞተ በኋላ ወደ ሲኦል መውረዱን መናገር የጥቅሱ ዐላማ አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስ የጌታን ቅርበት ለማስረዳት እጅግ ከፍ ያለ ቦታን (ሰማይን) እና እጅግ ዝቅ ያለ ቦታን (ጥልቅን) ተጠቅሟል። ሰማይን እና ሲኦልን (መቃብርን) በንጽጽር ማቅረብ ደግሞ የተለመደ አካሄድ መሆኑን ኢዮብ 11፥8 እና አሞጽ 9፥2 ያሳዩናል።
- “ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።” (ኤፌ. 4፥8-10)
አዲሱ መደበኛ ትርጕም እንዲህ ይገልጸዋል፤ “ታዲያ፣ ‘ወደ ላይʼ ወጣ ማለት ደግሞ ወደ ምድር ታችኛው ክፍል ወረደ ማለት ካልሆነ ምን ማለት ነው? ወደ ታች የወረደውም፣ መላውን ፍጥረተ ዓለም ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው።” ሐዋርያው ጳውሎስ ከመዝሙር 68፥18 ይህንን ሐሳብ ሲወስድ፣ ወደ ላይ የወጣውም ሆነ ወደ ታች የወረደው ያው አንዱ ጌታ መሆኑን ለማስረዳት ነው። ምክንያቱም ወደ ታች መውረድ ወደ ላይ ከመውጣት ይቀድማልና እግዚአብሔር ወልድ ሰው በመሆን (ሲሞት ሳይሆን!) ከሰማይ ወደ ምድር ባይወርድ ኖሮ፣ አሁን ወደ ሰማይ ባልወጣም ነበር። ወደ ላይ የወጣው አስቀድሞ የወረደው ራሱ ነው፤ ሌላ አይደለም። ይህም፣ “ከሰማይ ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም” ከሚለው የሐዋርያው ዮሐንስ አገላለጥ ጋር ይስማማል (ዮሐ. 3፥13)።
በምንባቡ የምናገኘውን የ“ምድር ታችኛ ክፍል” የሚል ማብራሪያ “ሲኦል” አድርጎ መውሰድ አጠራጣሪ አተረጓጐም ነው።[7] ይልቁኑ፣ ዋይን ግሩደም እንደሚናገሩት፣ ግሪክኛው “ታችኛው ክፍል፣ ይኸውም ታችኛው የምድር ክፍል” በሚል ተውላጠ ስማዊ ሐረግ መገለጹ አግባብ ነው።[8] እዚህ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ጌታ ወደ ሲኦል መውረዱን በአጽንኦት ወይም በግልጽ እያስተማረ አይደለም።[9] ጌታ ወደ ታች የወረደው በትስጉት ጊዜ ወይም ቃል ሥጋ ሲሆን ነው። ሲሞት አይደለም!
- “ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዐመፀኛዎች አንድ ጊዜ በኀጢአት ምክንያት ሞቷልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወህኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውሃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም።” (1ጴጥ. 3፥18-20)
ይህ ክፍል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ጠንካራ ምንባባት አንዱ ነው። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥም ብዙ አማራጭ ትርጓሜዎች ሲቀርቡለት ነው የኖረው። የዶክትሬት እና የማስተርስ መመሪቂያ ሥራዎችም ተሠርተውበታል።
ለመሆኑ ክርስቶስ የሰበከው ለማን ነው?
- ጌታ ኢየሱስ ሞቶ ከተቀበረ በኋላ፣ ወደ ሲኦል ወርዶ በብሉይ ኪዳን ለነበሩ ኀጥአን ወንጌል እንደ ሰበከላቸው የሚናገሩ ሰዎች አሉ። ይህ ግን “ሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት፣ ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው” ከሚያወራው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር ይጣረሳል (ዕብ. 9፥27፤ ሉቃስ 16፥26)። ሰዎች ከሞቱ በኋላ ወንጌል የሚሰበክላቸው መሆኑ ወይም ከሞት በኋላ ሌላ ዕድል መኖሩ ርቱዕ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ አይደለም። ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ “ስለዚህ ምክንያት ወንጌል ለሙታን ደግሞ ተሰብኮላቸው” እንደ ነበር (1ጴጥ. 4፥6) ቢጽፍም፣ ለእነዚህ ሰዎች ወንጌል የተሰበከላቸው በሕይወት ሳሉ (ከመሞታቸው በፊት) መሆኑ አግባብነት አለው።
- ክርስቶስ ለብሉይ ኪዳን ጻድቃን መስበኩን የሚያስቡ ሰዎችም አሉ። ምንባቡ ግን፣ “የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም።” የሚል በመሆኑ እነዚህ ሰዎች ጻድቃን እንዳልሆኑ ያመላክተናል።
- የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ “በወህኒ ለነበሩ ነፍሳት” የሚለውን፣ የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ “መናፍስት” ስለሚለው በዘፍጥረት 6 የተጠቀሱትን (የሰዎችን ልጆች ያገቡትን) መላእክት እንደሚመለከት አድርገው የሚናገሩ ሰዎችም አሉ። ደግሞም በኖኅ ዘመን የነበሩ ኀጥአን ተለይተው የተመረጡት ለምንድን ነው? ለሚለው የተቃውሞ ጥያቄ ይህ ሐሳብ በአማራጭነት ይቀርባል። ይህም ሐሳብ በተለይ ከመጽሐፈ ሄኖክ ጋር ተያይዞ የሚተነተን ነው።
የሰበከውስ መቼ ነው?
- ክርስቶስ የሰበከው በሞቱና በትንሣኤው መካከል ባለው ጊዜ ነው የሚል ሐሳብ አለ። ይህ ግን፣ “በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ” የሚለውን ሐሳብ በቅድሚያ መፍታትን ይጠይቃል፤ ምክንያቱም የሰበከውም በዚያው መንፈስ (“በእርሱም”) ነውና! “መንፈስ” የሚለው ቃል የክርስቶስን አካለ ነፍስ (የሰውነት መንፈሱን) የሚያመለክት ከሆነ፣ ክርስቶስ የተነሣው በአካለ መንፈስ ሊሆን ነው። ይህ ደግሞ እውነት አለመሆኑን ሉቃስ 24፥36-40 በግልጥ ይነግረናል። “በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው፣ “ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል” (ሮሜ 8፥11) የተባለለትን መንፈስ (የጌታን መለኮታዊ መንፈስ) ከሆነ ደግሞ፣ የሰበከውም “በእርሱ” ነውና “ጌታ በአካለ ነፍስ ሲኦል ወርዷል” ከሚለው ሐሳብ ጋር ጭራሹኑ ስምምነት የለውም።
በተጨማሪም ይህ አተረጓጐም አስቀድመን እንዳየነው፣ ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ሲሞት፣ መንፈሱን ለእግዚአብሔር ዐደራ እንደ ሰጠ እና አብሮት ከተሰቀለው ሰው ጋር በገነት እንደሚሆን ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይጋጫል። መንፈሱን ዐደራ ከሰጠ በኋላ መልሶ በመንፈሱ (በአካለ ነፍስ) ሲኦል ሄዶ ሰበከ ማለትስ እንዴት ይጣጣማል?
- ክርስቶስ የሰበከው ድል የመንሣት ስብከት ሲሆን፣ ይህንንም በተግባር የፈጸመው ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ በሚያርግበት ጊዜ ነው የሚል የትርጓሜ ሐሳብም ይቀርባል። ሐሳቡ፣ “እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኀይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ” ከሚለው ጥቅስ ጋር ይያያዛል (ቍ. 22)። “በወህኒ የነበሩ ነፍሳት” የሚለውን ግሪክኛው “መናፍስት” ስለሚለው፣ በዚህ ትርጓሜ መሠረት ከሆነ መናፍስት የተባሉት የወደቁ መላእክት ሲሆኑ፣ እነዚህም በዘፍጥረት 6 የተጠቀሱቱ ናቸው። ክርስቶስ ወደ ሰማይ በማረጉ፣ ድል የመንሣቱን መልእክት ለእነዚህ መናፍስት አስተላልፏል።[10] ይህ ደግሞ ከጌታ ወደ ሲኦል መውረድ ጋር አይገናኝም።
- ኖኅ በራሱ ዘመን ለነበሩ ኀጢአተኞች በሚሰብክበት ጊዜ፣ ክርስቶስ በመንፈሱ በኖኅ በኩል እንደ ሰበከ ይነገራል። በእርግጥም በምንባቡ ውስጥ ይህን ምልከታ የሚደግፉ አስረጅዎች አሉ። ኖኅን የጽድቅ ሰባኪ አድርጎ ጴጥሮስ በሌላ ስፍራ መግለጡ አንዱ ነው (2ጴጥ. 2፥5)፤ ይህም በላይኛው ምንባብ ውስጥ ከተጠቀሰው “መስበክ” የሚል ቃል ጋር ይስማማል።[11] ሐዋርያው ጴጥሮስ የክርስቶስ መንፈስ በብሉይ ኪዳን ነቢያት በኩል ይናገር እንደ ነበር አስቀድሞም አስረድቷል (1ጴጥ. 1፥10-11)፤ ስለዚህ ክርስቶስ በመንፈሱ በኩል በኖኅም ዘመን ለእነዚህ ሰዎች ተናግሮአል ማለት ይቻላል። ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን በተለያየ መልኩ ይገለጥ እንደ ነበረ ሌሎችም ማስረጃዎች አሉ (1ቆሮ. 10፥4-9)። በዚህም ላይ ዐውዱ ከዚህ ሐሳብ ጋር የተስማማ ነው።[12]
አስቀድሞም ለመግለጥ እንደ ተሞከረው ምንባቡ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ለተነሣው ርእሰ ጕዳይ መሠረት አድርጎ መውሰዱ አያስኬድም። እንዲያውም ክርስቶስ በኖኅ በኩል በመንፈሱ አስቀድሞ ለኀጥአን መስበኩን እና በዚያው መንፈስ ደግሞ አሁን ከሞት መነሣቱን የሚያትተው አገላለጽ ከሁሉም አማራጮች የተሻለ ትርጕም ይመስላል። ስለዚህ ክርስቶስ በሞቱና በትንሣኤው መካከል ሲኦል ወርዶ ነበር ለማለት ክፍሉ የተመቸ አይደለም።
እስካሁን እንዳየነው ከሆነ፣ የዘረዘርናቸው አራት ጥቅሶች፣ ስለ ክርስቶስ ሲኦል መውረድ በቀጥታ፣ በአጽንኦት ወይም በግልጽ አይናገሩም።
3. የሐዋርያት የእምነት መግለጫ
በዚህ ጽሑፍ ጅማሬ ላይ ለመግለጥ እንደ ተሞከረው፣ አሁን በእጃችን ያለው የሐዋርያት የእምነት መግለጫ ክርስቶስ ከሞተ በኋላ ወደ ሲኦል መውረዱን ይናገራል። ይህም በመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ለሚታየው ሥርዐተ አምልኮ እና በሌሎችም ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ለተያዘው ተመሳሳይ አቋም መሠረት ነው። ከላይ እንዳየነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጕዳይ በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ አይናገርም። ይህ ደግሞ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞተ በኋላ ወደ ሲኦል ወርዷል” የሚለው አቋም ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ በዚህ የሃይማኖት መግለጫ ላይ መመሥረቱን ሊያስረዳን ይችላል።
የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ ከኒቅያ እስከ ቍስጥንጥንያ፣ ከኤፌሶን እስከ ኬልቄዶን[13] ካሉት የእምነት መግለጫዎች ጋር በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት አለው። ሆኖም በተለያዩ ቦታዎች እና ዘመናት በመግለጫው ላይ አንዳንድ ነገሮች ይታከሉበት ስለ ነበር በልዩ ልዩ አካላት እጅ የሚገኘው የሃይማኖት መግለጫ የክርስቶስን ወደ ሲኦል መውረድ በሚመለከት ልዩነት አለው። የሃይማኖት መግለጫው በ200 ዓ.ም ጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን እስከ 650 ዓ.ም ድረስ የክርስቶስን ወደ ሲኦል መውረድ የሚናገር ክፍል አልነበረውም።[14] በአንዳንድ ስፍራዎች የተገኘው መግለጫ ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ወደ ሲኦል መውረዱን ቢገልጽም፣ መቀበሩን አይናገርም፤ በሮም እና በኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የነበረው መግለጫ ደግሞ መቀበሩን ይናገርና ወደ ሲኦል መውረዱን አይናገርም።[15] ይህም ወደ ሲኦል መውረድ እና መቀበር ተመሳሳይ ትርጕም እንዳላቸው ግንዛቤ መወሰዱን ያሳያል። ቀስ በቀስ ግን የሮም ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን መቀበር ከሚያመለክተው ቃል በኋላ ወደ ሲኦል መውረዱን አከለችበትና ጌታ መቀበሩን እና ወደ ሲኦል መውረዱን በአንድነት አጣምራ ያዘች።[16] ይህም አሁን ለገባንበት ውጥንቅጥ የራሱ መዋጮ አለው።
የሐዋርያት የእምነት መግለጫን ከሌሎቹ የእምነት መግለጫዎች ለየት የሚያደርገው ነገር አለ፤ ይኸውም የእምነት መግለጫውን ያረቀቀው (ያጸደቀው) ጉባኤ መቼ እና የት እንደ ተካሄደ እና ተሰብሳቢዎቹም እነማን እንደ ነበሩ አለመታወቁ ነው። የእምነት መግለጫው የአሁን መልኩን የያዘው በአንድ ወቅት በተደረገ የአብያተ ክርስቲያናት ውሳኔ ሳይሆን፣ ከ200-750 ዓ.ም ድረስ ቀስ በቀስ በተደረገለት ለውጥ ነው።[17] ከዚህ የተነሣ አሁን በተለያዩ አብያተ ክርስቲያና እጅ ያለው የሐዋርያት የእምነት መግለጫ የኢየሱስን ክርስቶስን ወደ ሲኦል መውረድ ከመግለጥ አኳያ አንድ ዐይነት አይደለም።
የኒቅያ የእምነት መግለጫ ስለ ጌታ ሞት፣ ቀብር፣ ትንሣኤ እና ዕርገት እንጂ፣ ወደ ሲኦል ስለ መውረዱ አይናገርም። መጽሐፍ ቅዱስም በግልጽ አያስቀምጠውምና ጌታችን ሲኦል ስለ መውረዱ የሚነገረው ሐሳብ ልክ አለመሆኑን እንገነዘባለን።
4. ክርስቶስ በሲኦል ተጨማሪ ዋጋ ከፍሏልን?
“የብልጽግና ወንጌል” የሚባለው ልዩ ወንጌል አራማጆች ርእሰ ጕዳዩን እጅግ ይለጥጡትና የጌታ ኢየሱስ የመስቀል ላይ ሞት ስርየት ሊያስገኝ እንዳልቻለ ያስተምራሉ። ከዚህም የተነሣ ጌታችን በሲኦል ውስጥ ለተጨማሪ ሥቃይ መዳረጉን (መከራ መቀበሉን)፣ ከዚያም በሲኦል ውስጥ የዘላለምን ሞት መሞቱንና በሲኦል ውስጥ ዳግመኛ መወለዱን እስከ መናገር ኑፋቄን ለማራመድ ይደፍራሉ። ይህንንም አስተምህሮ ኬንዮን፣ ኬኒት ሄገን፣ ኬኒት ኮፕላንድ፣ … ሲደጋግሙት ኖረዋል።[18]
አሁን አሁን ደግሞ ይህንን ኑፋቄያዊ አስተምህሮ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በጽሑፍ የሚያስተላልፉ ጸሓፊዎች ብቅ ማለት ጀምረዋል። (የኬኒዎን መጻሕፍት ወደ አማርኛ እየተተረጐሙ መሆኑን ሳንረሳ!) በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆነው ኤልሻዳይ አበራ “የመዋጀታችን ምስጢር” በሚል በቅርቡ ያሳተመውን መጽሐፍ እዚህ ጋ መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል።[19]
ይህ ሰው በዚህ መጽሐፉ እነዚህን ሐሳቦች አስተላልፏል። “አንዳንዶቻችን ሥራው በመስቀል ላይ ብቻ ያበቃ ይመስለናል። … ኢየሱስ ወደ ሲኦል የወረደበት ምክንያት እኛን ከመንፈሳዊ ሞት ለማዳን መንፈሳዊ ሞት መሞት ስለነበረበት ነው” (ገጽ 38)። “ክርስቶስ ወደ ሲኦል ወረደ፤ ለሰዎች የተሰጠውን የዘላለም ቅጣት ተቀብሎ ከእግዚአብሔር ተለየ፤ የዘላለምን ሞት ሞተ” (ገጽ 39)። “በመጀመሪያ ዳግመኛ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ነው። ከሙታን በኩር የሚለው ቃል የሚያሳየው ከዘላለም ሞት ወደ ዘላለም ሕይወት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሻገረው ክርስቶስ ኢየሱስ መሆኑን ነው። … ኢየሱስ እኛን ለመዋጀት በእኛ ኀጢአት ምክንያት ልጅነቱን አጥቶ /የዘላለም ሞት ሞቶ እንደነበር/ ያስረዳል። ነገር ግን ከሙታን በኩር ሆኖ በመነሣት ዳግመኛ ተወለደ” (ገጽ 46)። “ከዘላለም ሞት መጀመሪያ የተነሣ፣ የእግዚአብሔር ልጅነትን ዳግመኛ በመወለድ መጀመሪያ ያገኘ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ነው” (ገጽ 47)።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ትምህርቶች አንዳቸውም የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የላቸውም። ኢየሱስ ክርስቶስ በሲኦል የዘላለም ሞት መሞቱን መጽሐፍ ቅዱስ በጭራሽ አያስተምርም። “የዘላለም ሞት የሚገልጸው ከእግዚአብሔር ጋር መለያየትን ነው” ቢባል እንኳ፣ ጌታችን “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?” ያለው በመስቀል ላይ እንጂ በሲኦል አለመሆኑ ግልጽ ነው (ማር. 15፥34)። በተጨማሪም፣ “አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ” በማለት ጌታችን ነፍሱን ለእግዚአብሔር ዐደራ በመስጠቱ (ሉቃስ 23፥46) ከእግዚአብሔር ጋር የተቋረጠ ኅብረት ቢኖር እንኳ እንዳበቃ መናገር ይቻላል። ጌታችን “ከሙታን በኩር” ተብሎ የተጠራውም (ቈላ. 1፥18፤ 1ቆሮ. 15፥20)፣ በትንሣኤ አካል ከሞት ስለ ተነሣና ከዚህ በኋላም ስለማይሞት ነው። ከሞት የተነሡ ሌሎች ሰዎች ሁሉ (2ነገ. 4፥35፤ ሉቃ. 7፥15፤ ዮሐ. 11፥44፤ የሐዋ. 9፥36-41፤ 20፥7-12) ግን ተመልሰው ሞተዋል።[20] ጌታ ኢየሱስ በዚህ ትንሣኤው አማኞች ወደ ፊት ለሚሳተፉበት ትንሣኤ ቀዳሚ (በኩር) ሆኗል።
ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት “ተፈጸመ” ብሎ መናገሩ (ዮሐ. 19፥30) የኀጢአታችን ዋጋ ሙሉ በሙሉ መከፈሉን፣ እርሱ የሚከፍለው መከራም ማብቃቱን የሚናገር ነው (ዕብ. 1፥3፤ 9፥12፡25-28)።[21] ስለዚህ ከሞት ወዲያ ተጨማሪ መከራ የመቀበሉ አስፈላጊነት በአንድም ስፍራ ተገልጦ አናይም። ከዘላለም ሞት የዳንነው፣ ዕዳችን የተከፈለው፣ ከእግዚአብሔር ጋር የታረቅነውና ሰላም የወረደልን በመስቀል ሞቱ ነው (ቈላ. 1፥20፤ 2፥14፤ ኤፌ. 2፥16)። “ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፤ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም” እንደ ተባለ (ዕብ. 9፥22)፣ የኀጢአት ስርየታችን የተገኘውና ኅሊናችን የነጻው በክርስቶስ ክቡር ደም ነው (1ጴጥ. 1፥19፤ ኤፌ. 1፥7፤ ራእይ 1፥5፤ ዕብ. 9፥14)። ዛሬም ከኀጢአት የምንነጻው (1ዮሐ. 1፥7) እና ሰይጣንን የምናሸንፈው በዚሁ ደም ነው (ራእይ 12፥10-11)። ይህም የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን፣ በገዛ ደሙ የተዋጁ ሰዎች ስብስብ ያደርጋታል (የሐዋ. 20፥28)!
ይህም በመሆኑ፣ ክርስቶስ የኀጢአታችንን ዋጋ የከፈለው፣ መከራ የተቀበለው፣ የሞተው በሥጋ ነው ማለት ነው (1ጴጥ. 2፥24፤ 3፥18፤ 4፥1)፤ ጌታችን መንፈሳዊም ሆነ ዘላለማዊ ሞት አልደረሰበትም! እግዚአብሔር ወልድ ሰው መሆኑ በራሱ ውርደት ቢሆንም (ፊል. 2፥6-7፤ ገላ. 4፥4)፣ ከጌቴሴማኒ እስከ ቀራንዮ ያለው ጊዜ የውርደቱ (የመከራው) ጡዘት መሆኑ ግልጽ ነው። ቅዱሱ መጽሐፍ ጌታችን “እስከ መስቀል ሞት እንኳ” መታዘዙን እና ነውርን ንቆ የመስቀል ሞትን መታገሡን የጻፈው፣ መስቀሉ የመከራው እና የውርደቱ ጣራ መሆኑን ሲያሠምርበት ነው (ፊል. 2፥8፤ ዕብ. 12፥2)። ለጌታ ኢየሱስ ከመስቀል ሞት በኋላ የተቀበለው ውርደት ወይም መከራ አልነበረውም! በሲኦል መንፈሳዊ ሞትንም ሆነ የዘላለም ሞትን አልሞተም፤ እዚያም ውስጥ ዳግመኛ አልተወለደም። የእግዚአብሔር ልጅነቱም በሲኦል አልተወሰደበትም። ቅዱሱ መጽሐፍ፣ እነዚህን መናፍቃዊ ሐሳቦች በፍጹም አይደግፍም፤ ግለሰቡም ይህን የሚደግፍላቸው አንድም ጥቅስ አላቀረቡም።
የክርስቶስ ኢየሱስን የመስቀል ሞት ዋጋ የሚያሳንሰውንና ለኀጢአት ስርየት ያፈሰሰውን ደም የሚያራክሰውን ይህ ዐይነቱን አስተምህሮ ሐዋርያት አያውቁትም። ታሪካዊው ነገረ መለኮትም (ነገረ ክርስቶስም) ለዚህ አጋዥ የሚሆን ሐሳብ የለውም። እንዲሁ ደፋር አላዋቂዎች በድፍረት የሚያስተላልፉት ኑፋቄ በመሆኑ፣ አማኞችም ሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ከዚህ ዐይነቱ ትምህርት ራሳቸውንም መንጋቸውም በንቃት ሊጠብቁ ይገባል። እንደ ተለመደው በቸልታ ካለፍነው ግን፣ ቀስ በቀስ ሥር ሰድዶ ነገ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የድነት ትምህርት ማስተማርያ ሆኖ እንዳይገኝ ያሠጋል!
ልብ ያለው ልብ ይበል!
1. ይህ ትምህርት ከእነ ኬኒዎን ጀምሮ በብልጽግና ወንጌል አራማጆች የሚዘወተር ሲሆን፣ በአዲስ መልክ ሊያቀነቅኑት የሚሞክሩም አሉ። ለምሳሌ በጆሀንስበርግ ነዋሪ የሆነውና “የመዋጀታችን ምስጢር” የተሰኘ መጽሐፍ በቅርቡ ያሳተመውን ኤልሻዳይ አበራን መጥቀስ ይቻላል።
2. አማርኛ ማንበብ የሚመርጡ አንባቢዎች እነዚህን ጥቅሶች በአዲሱ መደበኛ ትርጕም ቢመለከቱ በግርጌ ማስታወሻ ተጨማሪ ማብራሪያ ያገኛሉ።
3. ወደ እንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጕሞች ስንመጣም፣ ቃል ላይ ትኵረት የሚያደርገው ESVም ሆነ ሐሳብ ላይ ትኵረት የሚያደርገው NIV እነዚህን ጥቅሶች “መንፈስ” በማለት ነው የተረጐሟቸው። KJV እና አዲሱ መደበኛ ትርጕምም ይህንኑ መሥመር ተከትለዋል።
4. በተመሳሳይ መልኩ ESV፣ NIVም ሆነ KJV ይህንኑ ነው የሚደግፉት።
5. NIV Study Bible (Grand Rapids: Zondervan, 2002), 1761.
6. ESV Study Bible (Wheaton: Crossway Bibles, 2007), 2174-75.
7. L. Berkhof, Systematic Theology (Grand Rapids: Eerdmans, 1979), 341.
8. ዌይን ግሩደም (ትርጕም)፤ ስልታዊ ነገረ መለኮት፤ ቅጽ 1፤ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መግቢያ (አዲስ አበባ፤ ኤስ አይ ኤም፤ 2003) ገጽ 660።
9. ኮሊን ማንስል፤ ትምህርተ ክርስቶስ፡ አጠቃላይ የነገረ መለኮት ትምህርት፤ 2ኛ መጽሐፍ (አዲስ አበባ፤ 1999) 200፤ NIV Study Bible, 1835.
10. NIV Study Bible, 1933.
11. ESV Study Bible, 2410.
12. ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 2410።
13. የኬልቄዶን መግለጫን ካቶሊካውያን፣ ፕሮቴስታንቶችና የምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን ሲቀበሉት፣ ኦርየንታል ኦርቶዶክሳውያን አይቀበሉትም።
14. ግሩደም፤ ስልታዊ ነገረ መለኮት፤ ገጽ 657።
15. Berkhof, Systematic, 340-41.
16. ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 341።
17. ግሩደም፤ ስልታዊ ነገረ መለኮት፤ ገጽ 656።
18. ግርማዊ፤ የብልጽግና ወንጌል (አዲስ አበባ፤ ኤስ አይ ኤም፤ 2008) ገጽ 22-26።
19. ኤልሻዳይ አበራ፤ የመዋጀታችን እውነታዎች (ጆሀንስበርግ፤ 2014)።
20. NIV Study Bible, 1854.
21. ESV Study Bible, 2068.