You are here: HomeSermonግርዶሽ ወይስ ነጸብራቅ?

ግርዶሽ ወይስ ነጸብራቅ?

Written by  Wednesday, 19 April 2017 02:26

ፊደል ላልቆጠረ፣ አስኳላ ላልደፈረ ገጠሬ “ጨረቃ እኮ የራሷ ብርሃን የላትም!” ቢባል አሻፈረኝ ሊል፣ ከባሰም ቆመጥ ሊያነሳ ይችላል። ታዲያ ማን ይፈርድበታል? በጨቅላነቱ “ጨረቃ ድንብል ቦቃ . . .” እያለ የዘመረላትን፣ በወጣትነቱ ምሽቱን ያደመቀችለትን፣ በውድቅት ጨለማውን ያፈካችለትን ጨረቃ የራሷ ብርሃን የላትም ቢባል እንዴት ሊዋጥለት ይችላል? እውነቱ ግን ያ ነው። ጨረቃ ለራሷ በቆፈን የተቆራመደች ቀዝቃዛ ፈለክ (ፕላኔት) እንደሆነች ለዘመናት ያጠኗት ይመሰክራሉ።

 

ምድር በምትገኝበት የሕዋ ንፍቀ ክበብ ብቸኛዋ የብርሃን ምንጭ ፀሐይ ናት። ምድር በራሷ ዛቢያ በምታደርገው ዙረት ሳቢያ ቀንና ሌሊት ይፈራረቃሉ። ጀርባችንን ለፀሐይ ስንሰጥ ይጨልምብናል። በምሽት የፀሐይን ብርሃን በቀጥታ ማግኘት ባንችልም በተዘዋዋሪ እናገኛታለን። ጨረቃ የፀሐይን ብርሃን ተቀብላ በማንፀባረቅ እኛን የምድሮቹን ታገለግላለች።

 

ሆኖም ጨረቃ በዘመናት ውስጥ አልፎ አልፎ የሚከሰት አንድ ጣጣ አላት። ከፀሐይ ብርሃን ተቀብላ ሌሊታችንን ማፍካቷን ትተውና በፀሐይና በምድር መካከል ተደንቅራ የፀሐይን ብርሃን በመጋረድ ቀናችንን ታጨልማለች። ይህንንም የፀሐይ ግርዶሽ ወይም ኤክሊፕስ ብለን እንጠራዋለን።

 

ይህ ተፈጥሯዊ ክስተት ለእኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ለምናምንና ሕያው እግዚአብሔርን ለምናገለግል ትልቅ መልዕክት አለው። ጨረቃ የራሷ ብርሃን እንደሌላት ሁሉ ማንኛውም አገልጋይ የራሱ የሆነ አንዳች ነገር የለውም። የእኔ ጸጋ፣ የእኔ ቅባት፣ የእኔ ቤተክርስቲያን፣ የእኔ ሕዝብ የሚባል ነገር የለም። የተጠራነው ተግተን ፊቱን እየፈለግን ከእርሱ የተቀበልነውን ብርሃን በጨለማ እንድናበራና ክብሩን እንድናፀባርቅ ብቻ ነው።

 

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ የአባቱን ፈቃድ ሊፈጽም በሥጋ በመጣ ጊዜ ያደረገው ይህንን ነው። የእግዚአብሔርን ክብር በጨለማ ላሉ በማንፀባረቅ የማይታየውን እግዚአብሔርን በቃሉና በሥራው ተረከው። ለዚህ አይደል የዕብራውያን መልዕክት ጸሐፊ፦

 

“እርሱም የክብሩ መንፀባርቅና የባሕሪው ምሳሌ ሆኖ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” (ዕብ. 1፥2) የሚለን።

 

እኛም የተጠራነው የክርስቶስን ብርሃን ተቀብለን እንድናፀባርቅ እንጂ ክርስቶስን ጋርደን ራሳችንን አግንነን፣ እንዳልተቀበለ ኮርተን፣ ሁሉን ለራሳችን አጋብሰን ጭላንጭሉንም እንድናደበዝዝ አይደለም። ቅዱስ ቃሉ

 

“እኛ ግን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስታወት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ ዘንድ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን” (2 ቆሮ. 3፥18)

 

እንደሚል ለማንፀባረቅ ተጠርተናል። ሆኖም በዘመናችን ነፀብራቅ ሳይሆን ግርዶሽ እየበዛ ያለ ይመስላል። አገልጋዮች በጨለማ ያሉ ሰዎች የማይታየውን የእግዚአብሔርን ብርሃን እንዲያዩ ከማገዝ ይልቅ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ገብተው እኔን እዩኝ ካሉ እንኳን ጨለማ ሊያበሩ ቀኑን ያጨልማሉ። ያኔ ነው መንፈሳዊ ኤክሊፕስ ወይም የእግዚአብሔር ግርዶሽ የሚከሰተው። መጋረድ የሉሲፈር እንጂ የክርስቶስም ሆነ የእውነተኛ ተከታዮቹ ተግባር አይደለም። አገልጋዮች ከዚህ ክፋት ለመመለስና ንስሐ ለመግባት ካልወደዱ አልፎ አልፎ በተፈጥሮ እንደሚከሰተው ጨረቃም በተራዋ በምድር ተከልላ ደም እንደምትለብስ የሚጋርዱ ሁሉ የመጋረድ እጣ ፈንታ ይደርስባቸዋል። በፍርድም ሥር ይወድቃሉ።

 

ስለዚህ ክብሩን መጋረዳችንን ትተን ክብሩን በማንፀባረቅ እንትጋ።  

 

ጸሎት

ጌታ ሆይ ከእኔ የሆነ አንዳች ነገር የለም። በእኔ ያለ መልካምነት ካለ ከአንተ የተቀበልኩት ነው። ስለዚህ ክብርን ሁሉ ለአንተ እሰጣለሁ። አሁንም የማያልቀውን ጸጋና ክብርህን ከአንተ እየተቀበልሁ ለሌሎች እንዳበራ እርዳኝ። ስትጠቀምብኝ አንዳች የሆንኩ መስሎኝ እንዳልኮራ። በአንተና በሰዎች መሐል ገብቼ፣ ክብርህን ጋርጄ በፍርድ ሥር ከመውደቅ ጠብቀኝ።

 

 

Read 14177 times Last modified on Wednesday, 19 April 2017 02:46
Yared Tilahun

President, Golden Oil Ministry

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 27 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.