‹‹ አጥብቆ ጠያቂ የእናቱን ሞት ቢረዳም›› እውነቱን አውቆ እርሙን ማውጣት፣ ማድረግ ያለበትንም አስተውሎ ማድረግ ይሻለዋል፡፡
የእኛ አገር ነገር አደናጋሪ፣ አሳሳቢ፣ አስጨናቂ፣ አጠያያቂ ከሆነ ሰነበተ፡፡ በአንድ ወገን ሲቃና በሌላ ወገን ይደረመሳል፣ ዛሬ በሰለ ሲባል አድሮ ቃሪያ ይሆናል፡፡ እፎይታ የሩቅ ህልም እየመሰለ ሄደ፡፡ ውጥረትና ሁካታ የወትሮ ልብስ ሆኑ፤ ጣርና ሲቃ አየሩን ሞሉት፡፡ ለምንድነው ይህ የሚሆነው? ምን ቢሆን ነው የሚስተካከለው? መቼ ነው ይህ አገር አደብ የሚገዛው? ብርቱ ጥያቄ ልቦናችንን ይገዘግዛል፡፡ እንደ አገር ሁሉ ቤተክርስቲያንም እንደታመመች እንዳቃሰተች አለች፡፡ የብርሃን ማማ እንድትሆን የተጠራች፣ የተስፋ ቋት እንድትሆን የምንጠብቃት ይህች የክርስቶስ አካል ኩራዟ እየተስለመለመ፣ ጎተራዋ እየተመናመነ የሚሄድ ይመስላል፡፡
ለምን ይህ ሁሉ ሆነ?
የዚህ መጣጥፍ ርዕስ ከመጽሐፈ መሳፍንት ምዕራፍ 6 የተቀዳ ነው፡፡ ጌዴዎን ብርቱ ገበሬ እንደነበር ከትጋቱ እናስተውላለን፤ በጠላት በተዋከበ አገር ውስጥ ተደብቆም ቢሆን፣ ጉድጓድ ገብቶም ቢሆን ስንዴውን ይወቃል፣ አላረፈም፣ እጅ አልሰጠም፡፡ በሥራ ቦታው የተገለጠለት መልአክ ከጌዴዎን አስተሳሰብ ጋር የማይገጥም ከፍ ያለ ነገር ይናገራል፡፡ ‹‹ አንተ ጽኑዕ፣ ኃያል ሰው ፣ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፡፡››
የመልአኩ ዐዋጅ እና የመሬቱ እውነታ አልገጣጠም ያለው ጌዴዎን ብርቱ ጥያቄ ጠየቀ፡፡‹‹ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? ለምን የምድያም መጫወቻ ሆንን? ለምን ዘወትር በፍርሀት እና በሰቀቀን እንኖራለን? ለምን መቅኖ ቢስ ተንከራታቾች፣ የዋሻ እና የጉድጓድ ነዋሪዎች ሆንን? ስንት ታሪክ እየተተረከልን፣ ስንት ታምራት እየተነገረን አሁን ያለንበት ሰቆቃ ውስጥ ለምን ወደቅን?
የጌዴዎንን ታሪክ ዙሪያ ገባ ስናጤን መልሱ አጅግም ውስብስብ አይደለም፡፡ ሕዝበ እስራኤል ከባርነት ያወጣቸውን አምላክ በሌሎች አማልክት ተክተውታል፡፡ ‹‹ባዕዳን አማልክትን አታምልኩ›› ያላቸውን የታዳጊያቸውን ቃል አልሰሙም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ በመከራም ውስጥ ሆነው ትዕቢታቸው እና ‹‹ ከእኛ በላይ ላሣር›› የሚለው መፈክራቸው አልተለወጠም፡፡ ‹‹ እስራኤል እጄ አዳነኝ ብሎ እንዳይታበይብኝ የሰራዊቱን ቁጥር ቀንስ›› ብሎ እግዚአብሔር ጌዴዎንን ያዘዘው የልባቸውን ዐውቆ ነው፡፡ ከድል በኋላ እንኳ አንዳንዶቹ የታሪክ ሽሚያ ውስጥ ገብተው ‹‹ እኛን ሳትጠሩን ለምን ዘመታችሁ?›› እስኪሉ ድረስ ጉረኞች ነበሩ፡፡
በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ ሌሎች ጥያቄዎች አሉ፡፡ ‹‹ ፀሎት የማትመልስ ከሆነ ለምን ጾምን? ለምንስ ጸለይን? የሚሉ፡፡ ‹‹ አንተን ፈልገን እራሳችንን ያዋረድነው ፋይዳው ምንድነው? የሚሉ፡፡ ለእነዚህም መልሱ ሩቅ አይደለም፡፡ አስመሳይ ሀይማኖተኞች፣ ጸሎት አሳማሪ፣ ክፉ ሥራ ሠሪ ሆነው የተገኙ ናቸው፡፡ ግብዝ ሃይማኖተኝነት ከባዕድ አምልኮ አይተናነስም፡፡ ይጾማሉ፣ እንደ እንግጫ እራሳቸውን መሬት ላይ ያነጥፋሉ፤ ግን ከጸሎት ሲነሡ ያው የራሳቸውን ፍቃድ ይፈጽማሉ፡፡ ምንም ለውጥ የለም፡፡ ከጾምና ከጸሎት ሲመለሱ በግፍ ጡጫ ይማታሉ፣ ፍትህ ማጓደል፣ እብሪት ና ንፉግነት ያጠመቀው የኑሮ ዘይቤያቸው በሀይማኖተኝነት ካባ ተጀቡኖ ይጎማለላል፡፡
አምላክ እንዴት ይስማ?
የዕዝራ-ነህምያ ዘመን ሰዎች ደግሞ የገቡበት አስጨናቂ በደል ድብልቅነት ነበር፡፡ የተመረጠው ሕዝብ ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፣ከርኩሰታቸው እና ከጸያፍ ሥራቸው ጋር ተባበረ፡፡ ልዩ ማንነቱን አሽቀንጥሮ ጥሎ ያው እንደጀማው፣ ያው እንደሰፈሩ፣ ያው እንደጎረቤቱ ሆነ፡፡ ‹‹ ፊቴን ወዳንተ ለማንሣት አፍራለሁ፣ እፈራማለሁ›› እስኪል ድረስ የካህኑ የዕዝራ ለቅሶ ከባድ ነበር፡፡ ለአገራዊ ችግሮቻችን ብዙ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ምናልባትም ሥነልቦናዊ ትንታኔ ሊሰጥ እንደሚችል አይጠፋኝም፡፡ሁሉም በአግባቡ ቦታ ይኖረዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ እግዚአብሔር ሰዎች መሰረታዊ ምክንያቱን ቆፍረን ማግኘት ይገባናል እላለሁ፡፡
እንደ ሕዝበ እስራኤል ሆነንስ ቢሆን?
- በነባር ባህል ስም፣ በአባቶቻችን ቅርስ ስም ባዕድ አምልኮን አንግሠንስ ቢሆን?
- ዐደባባዮቻችን ለሌሎች አማልዕክት መሠዊያ መሥሪያ ሜዳ ሆነውስ ቢሆን?
- በየልባችን ጓዳ የፍቅረ ነዋይ፣ የአውስቦ፣ የዝና ጣዖታት እያባበለን ቢሆንስ?
- በዘር፣በታሪክ ትምክህት ልባችን ተደፍኖ ዕብሪት እና ትዕቢት አፍኖን ከሆነስ?
- በዝሙት፣ በርኩሰት፣ በከንቱ ፈንጠዝያ፣ በዓለማዊ ልማድ ተጠፍረን፣ እየፀለይንም፣ እየጾምንም እዚያው ረግረግ ውስጥ ተዘፍቀን እንደሆነስ?
- በየቤታችን ፣በየመሥሪያ ቤታችን ግፍ እየፈፀምን፣ፍትህ እያዛባን ማስነን እንደሆነስ?
- ይህን ሁሉ በክርስትና ካባ፣ በጮሌ ቋንቋ ሸፋፍነን እየተሳሳቅን ቢሆንስ?
- የጥላቻ መርዝ በሠራ አካላችን ተሰራጭቶ በቁም የሞትን ሬሳ አድርጎንስ ቢሆንስ?
ይህን ሁሉ የምጠይቀው በትህትና ነው፤ተጨንቄ ነው፤ ራሴንም እዚያው ውስጥ እየተመለከትኩ ነው፡፡ ወገኖች‹‹ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን?›› ብሎ መጠየቅ ነውር ነው እንዴ? አምላክ ጥያቄ አይፈራም፤ ለመልስም አይቸገርም፤ ስለዚህ በቅንነት እንጠይቅ፡፡
‹‹ አሁን የእኛ ኀጢአት ከሌሎች አገሮች እና ሕዝቦች በደል በልጦ ነው እንዴ?›› ቢባልስ?‹‹ እግዚአብሔርን ሽምጥጥ አድርገው የካዱት፣የሰደቡት ሕዝቦች ተመችቷቸው ይኖሩ የለ? እኛ ከእነርሱ ብሰን ነው?›› ወዳጆቼ መጽሐፍ ምን ይላል---- ‹‹ ለእያንዳንዱ እንደሥራው እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ›› የሚል የምድር ሁሉ ዳኛ እንዳለ ይነግረናል፡፡ ለማን፣ መቼ ምን እንዳቆየለት አናውቅም፤ ብያኔው በእጁ ነው፡፡ ታሪክም በአንድ ትውልድ ዕድሜ አይቋጭም፡፡ እስራኤል የወጓቸው የአሞራውያን ኀጢአት ጽዋ እስኪሞላ አራት መቶ ዓመት ተጠብቋል፡፡ የዘመንን እና የፍርድ ነገር በጻድቁ አምላክ አጅ ነው፡፡ የእነርሱን ለእነርሱና ለእውነተኛው ዳኛ ትተን በራሳችን ጉዳይ ላይ ማትኮር ይሻለናል፡፡
ይህስ ይሁን----- መዳኛ፣ መቃኛ መንገድ የለም ወይ? ካልን ግን ለሁሉም አጥጋቢ መልስ ተሰጥቷል፡፡ ጌዴዎን ከመዝመቱ በፊት አባቱ የሠራውን የበዓልን መሠዊያ እንዲያፈርስ ተጠየቀ፡፡ በኢሳይያስ ትንቢት የተጠቀሱት ሰዎች የግፍ ሥራን ትተው በርኅራኄ እና በጽድቅ እንዲኖሩ ተነገራቸው፡፡ የዕዝራ-ነህምያ ዘመን የምርኮ ተመላሾች እራሳቸውን ከድብልቅ ሕዝብ እንዲያጠሩ ታዘዙ፡፡ ለእኛም ይኸው ነው፡፡ ቁርጠኛ የመመለስ እርምጃ መውሰድ፡፡
‹‹ በዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደንጋት ይበራል፣ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፣ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፣ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል፡፡ የዚያን ጊዜ ትጣራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሀል፣ትጮኻለህ እርሱም እነሆኝ ይላል------;
(እባካችሁ ኢሳይያሰ 58 ን አንብቡ እና የእግዚአብሔርን ደግነት አስተውሉ፡፡)
በመካተቻው ግን እስከዛሬ ከተጠየቁት ‹‹ ለምን)›› ኦች ሁሉ የላቀውን ‹‹ለምን›› የመልሶች ሁሉ ዐውራ የሆነውንም መልሱን መናገር አለብኝ፡፡ ጠያቂው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነበረ፡፡ ‹‹ አምላኬ ፣ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?›› ሰበቡም (መልሱም) የእኔ እና የእናንተ ኀጢአት ነበረ፡፡ መትረፊያውም መስቀሉ ነበረ፤ ነውም፡፡ ለዓለሙ ሁሉ ‹‹ለምን››ታ የእግዚአብሔር ቁርጥ መልስ የክርስቶስ ኢየሱስ መስቀል ነው፡፡ ወዳጆቼ ሆይ በመስቀሉ አምባ ውስጥ ተገን እናገኛለን፡፡ ሙጥኝታችን፣ ትምክህታችንም ራቁቱን የተሰቀለው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
እኛን ያድነን ፤ አገራችንን ይፈውስልን፤ ቤተክስቲያንንም ያድስልን፡፡