You are here: HomeOpinionsቤን ሒን አጎቴ ነው፤ … የብልጽግናው ስብከት ግን ለኔ አልሆነም!

ቤን ሒን አጎቴ ነው፤ … የብልጽግናው ስብከት ግን ለኔ አልሆነም!

Written by  Tuesday, 31 October 2017 11:20

የዛሬ አስራ አምስት አመት ገደማ ከጌታ ጋር ባለኝ ሕብረት እና የአገልገሎት ተጽዕኖ በመተማመን ከግሪክ አቴንስ ወጣ ብሎ ባለ ባህር ዳርቻ በኩራት እኖር ነበር። በወንጌል አገልግሎት ሰበብ በግል ጀቶች አለምን እየዞርኩ፣ ገንዘብ ሊገዛው የሚችለውን የቅንጦት ኑሮ ኖር ነበር። ከተመቻቸ በረራ እና በግል ሼፋችን ከተሰራ እና ከምወደው ምግብ(ላዛኛ) በኋላ፣ ለቀጣይ አገልግሎታችን እንድንሰናዳ በታወቀውና በተከበርው ላጎሲ የእንግዶች ማረፊያ እናርፋለን። ፪ ሺ ስኩዬር ጫማ ክፍት ስፍራ ያለው፣ ውቅያኖሱን በጉልህ የሚያሳይ ድንቅ እይታ ያለው፣ ደረጃውን የጠበቀ የመዋኛ ገንዳ ያለው የራሴው የጉራ ቪላም አለኝ። በውሃው ጠርዝ ላይ ባለ ከፍ ያለ ድንጋይ ላይ ቁጭ ብዬ የምኖረውን ሕይወት አጣጥም ነበር። በዚህ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስን አገለግልና እርሱ ቃል የገባልንን የተደላደለ ሕይወት እኖር ነበር።

 

ይህ የባሕር ጠረፍ በተመሳሳይ ሐዋሪያው ጳውሎስ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ለማስፋፋት በመርከብ ይጓዝበት የነበረበት ከሚስያ ባሕር አንዱ አካል እንደነበር በጥቂቱም ቢሆን አውቃለው። አንድ ነገር ብቻ ነበር የሚለየን፤ እኛ የጳውሎስን አይነት ወንጌል አንሰብክም ነበር።

 

ቅንጦተኛ የአኗኗር ዘይቤ

በሒን ቤተሰብ ግዛት ውስጥ ማደግ ማለት፣ በተከበረ ቤተሰብ እና ማፊያ መሐል እንደመኖር ማለት ነው። የእኛ የአኗኗር ዘይቤ ቅንጦተኛ፣ ታማኝነታችን የሚከበር እና የወንጌላችን አይነት ደግሞ ትልቅ ቢዝነስ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌላችን አንዱ አካል ይሁን እንጂ ከነገስታት ንጉሥነቱ ይልቅ እንደ ምስራቃዊ አስማት ጂኒ ነበር። ከእርሱ ጋር በሚገባ ከተጣበቅህ (ገንዘብ ብትለግስ እና በቂ እምነት ቢኖርህ)መንፈሳዊ ውርስ ማግኛ በር ይከፈትልሀል። “የእግዚአብሔር አላማ ለራሱ ክብር ሳይሆን ለእኛ ጥቅም ነው። ጸጋው ከኃጢአት ነጻ ሊያወጣን ሳይሆን ሀብታም ሊያደርገን ነው፤ ለእኛ የሰጠን የተትረፈረፈ ኑሮ ገና የሚመጣ አይደለም፤ አሁን ነው!” ብለን ብልጽግና ወንጌልን ኖረናል።

 

አባቴ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ቫንኮቨር በምትባል ከተማ ውስጥ በትንሽ ቤተክርስቲያን ውስጥ መጋቢ ነበር። በጉርምስና እድሜዬ ላይ እያለው በወር ወደ ሁለት ጊዜ ከአጎቴ ቤን ሒን ጋር ለስብከት በየቦታው ይጓዝ ነበር። ታዲያ የብልጽግና ስነ መለኮት በአስደናቂ ሁኔታ ብድራቱን ከፈለን። ፲ ሺ ስኩዌር ጫማ ስፋት ያለው፣ የተከለለ እና የራሱ በር ያለው እልፍኝ አዳራሽ ቤት ውስጥ እንኖራለን፤ ሁለት ማርሴዲስ ቤንዝ የቤት መኪኖች እንነዳለን፤ ለአይን በሚማርኩና ትንግርት በሚሆኑ መዳረሻዎች ላይ እንዝናናለን። ውድ የሆኑ መገበያያ ቦታዎች ላይ እንገበያያለን። በዛ ላይ ደግሞ በሁለት ሚሊዮን ዶላር የቤንዝ ካምፓኒ ከጦር መርከብ ስራ ጋር ውህደት በፈጠረባት፣ ካሊፎርኒያ ዳና ፖየንት ላይ የውቅያኖስ እይታ ያለው መኖሪያ ቤት ገዝተን፣ ተትረፍረፈን ተባረከን እንኖር ነበር።

 

በእነዚህ አመታት ከውስጥም ከውጪም ብዙ አይነት ትችቶች ደርሰውብናል። ዴት ላይን ኤን.ቢ.ሲ፣ ዘ ፌዝ እስቱት (የካናዳውያን የዜና መርሐግብር) እና ሌሎችም ሾዎች የተጠና ስራ ሰርተውብናል። በጣም የታወቁ የአንዳንድ ሚንስትሪ መሪዎች በየሬድዮው ሕዝቡን ከእኛ ትምህርት ራሱን እንዲጠብቅ ሲመክሩ፣ በወቅቱ የየአብያተክርስቲያናቱ የአጥቢያ መጋቢያን የነበሩ ሁሉ ሒን ካለበት ምስባክ ራሳቸውን እንዲያጠሩ ለምእመናኑ ሲመክሩ እና ሲገዝቱ፣ እኛ እንደ ጳውሎስ እና እንደ ኢየሱስ እየተሰደድን ያለን እና ተቺዎቻችን በእኛ መባረክ እየቀኑብን እንዳለ አድርጌ ነበር የማምነው።

 

በቤተሰባችን ትችትን አንቀበልም። አንድ ቀን፣ በካንሰር ምክንያት ጠጉሯ የተመለጠውን፣ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ልጃገረድ፣ ሄደን እንፈውሳት እንደሆን ብዬ አባቴን ጠየኩት። ”ቤቷ ድረስ ሄደን ከምንፀልይላት እዚው ብንጸልይ ይሻላል“ ብሎ መለሰልኝ። የሐዋሪያቱ አይነት ስጦታ ካለን እነሱ ያደረጉትን ማድረግ የለብንም እንዴ? ብዬ ራሴን ጠየኩ። በዚህ ነጥብ ላይ፣ የእኛን የመፈወስ ስጦታ ጥያቄ ውስጥ አልከተትኩም፤ ነገር ግን የእኛን አለመነሳሳት ተጠራጠርኩት። እኛ ፈውስ ምናደርገው ሕዝብ ”በትክክለኛ እምነት“ ሆ ብሎ በሚቀርብበት፣ እጅ መንሻ ይዞ በሚመጣበት እና የሙዚቃ ድባብ በደራበት በትልቅ ክሩሴድ ላይ ብቻ ነው።

 

ጥርጣሬ ይድበሰበሳል። ስለ አልተሳኩ የፈውስ ሙከራዎች የተማርኩት፣ "ያ የሕመመተኛው ችግር ነው” የሚልን ማስተባበያ ነው። እግዚአብሔርን ተጠራጥሮታላ! ስለ ማይተረጎም ልሳን ስጠይቅ የተነገረኝ ”መንፈስን አታጥፋ፤ እሱ ያሻውን ማድረግ ይችላል!“ ተብሎ ነው። የእኛ ትንቢቶች ለምን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጣረሳሉ? ስል ”እግዚአብሔርን በአንድ ሳጥን ውስጥ አስቀምጠኽ አትወስነው“ ይሉኛል። ግና ከጥያቄዎቼ ይልቅ ቤተሰቦቼን አምናቸዋለሁ፤ ምክንያቱም ስኬታማዎች ነበርና! በአስር ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ይከተሉናል፤ ሚሊየኖች ደግሞ አጎቴን ለመስማት ስታዲየሙን ይሞላሉ፤ ሕመምተኞችን እንፈውሳለን፤ ተአምር እናደርጋለን፤ ለዝነኞች እጆቻችንን እንጭናለን፤ ረብጣ ገንዘብም እናገኛለን። ስለዚህ ግድ እግዚአብሔር ከእኛ ወገን ሊሆን ይገባል!

 

ወደ ኮሌጅ ከመግባቴ በፊት ለአንድ አመት ያህል የቤን ሒን ሚንስትሪ ውስጥ ደጋፊ (ማለትም በመንፈስ የሚወድቁትን ሰዎች የሚደግፍ ሰው) እና የግል ረዳቱ ሆኜ ተቀላቀለቅዬ ነበር። ይህ በእኛ ቤተሰብ፣ የሐይማኖቱን ባሕል እና ወግ ማስተላለፊያ መንገድ ነበር። እንደኔውም ሁሉም የወንድሞቹ ልጆች የተወሰነ ያህል ለቤን ሒን ይሰራሉ። ለቤተሰቡ እምነት እና አክብሮት እንዲኖረን ማስተማሪያ ነበር። ያ አመት እንደ ዲደን (አውሎ ንፈስ) የቅንጦት ማማ ላይ በአንዴ ወጣሁ፤ በ፳፭ ሺ ዶላር የተከበረ ቤተሰብ እራት ግብዣ ላይ የሚለበስ ሱፍ ከዱባይ ገዛው፤ ግሪክ ውስጥ አለ ከተባለ ከባሕር የሚታከክ የእንግዳ ማረፊያ (ሪዞርት) ላይ ተንፈላሰስኩኝ፤ የስዊዲሾች ሰንሰለታማ ተራራ ላይ ወጣሁ፤ ጣሊያን ኮሞ ሐይቅ ላይ ቪላ ገዛሁ፤ አውስትራሊያ በሚገኘው ወርቃማው ባሕር ዳርቻ ሆኜ ጸሐይ ሞቅሁ፤ በእውቁ ገበያ በሀሮድ ለንድን ደማቅ ነገሮችን ተገበያየው፤ በተደጋጋሚ ደግሞ እስራኤልን፣ ሃዋይን እና በአካበቢው ያለውን ሁሉ ጎብኘሁ። ክፍያችን በጣም ትልቅ ነበር፤ በራሳችን የግል ጀት እንበራለን። በራሴ ልክ፣ ዲዛይን እና ምርጫ የተሰፋ ሱፍ ማሰራት ችያለው። ብቻ የሚጠበቅብኝ ነገር ሰዎችን ሲወድቁ መያዝ እና መንፈሳዊ መምሰል! ይሄው ነው!

 

ሕይወቴን የቀየረው ጥቅስ

ከኮሌጅ ተመርቄ ወደ ቤት ከተመለስኩኝ በኋላ ባለቤቴ ክርስቲንን አገኘዋት። እግዚአብሔር እሷን ተጠቅሞ ወደ ድነት መንገድ ያመጣኛል ብዬ አስቤ አላውቅም። በርግጥ እኔና ቤተሰቦቼ አፍዋን አውጥታ መናገር ስለማትችል (ድዳ ስለሆነች)እንጨነቅ ነበር። ይሄን ችግር ለመፍታት በቤን ሒን ክሩሴዶች ላይ እንድትሳተፍ ነገሮች አመቻቸን፤ ምንም የተፈጠረ ለውጥ የለም። በቀጣይም ቫነኮቨር የሚገኘው እኔ ያደኩበት አጢቢያ ቤተ ክርስቲያን ወሰድኳት፤ ያም አልሰራም። በመጨረሻም በአንድ የወጣቶች ጉባኤ ላይ አንዳንድ ስልጠናዎችን ወሰደች፤ ነገር ግን ከጥቂት የፊደል ግሩምጉምታ በሰተቀር ምንም መናገር አልቻለችም። ስለ እውነት ለመናገር የሆነ ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር ላገባት እንደማልችል ነበር ሳስብ የነበርው።

 

ታዲያ አንድ ቀን፣ ከዚያ ቀደም አይቼ የማላውቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ በእጇ አመላከተችኝ። ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጉማሉን? የሚለው በ፩ ቆሮ ፲፪÷፴ ላይ ያለው ጥቅስ ነበር። ከውስጤ ነበር የተናወጥኩት። ሁሉም በልሳን እንደማይናገሩ፣ እንደ ቀን ብርሀን ነበር ወለል ብሎ የታየኝ። ወዲያው ነበር ይሄ ጥቅስ ተጽእኖ ማድረግ የጀመረው፤ ዘመን ያስቆጠሩ ልማዶቼና እምነቶቼ በመጽሐፍ ቅዱስ ሚዛን ተመዝነው ወደቁ። የአግዚአብሔር አላማ እኔን ደስተኛ፣ ጤነኛና ሀብታም ለማድረግ ነው የሚለው እምነቴ ከዚህ በኋላ ሊቀጥል አልቻለም። በዛ ፈንታ እኔ ከእርሱ ላገኝ ከምችለውን ጥቅም በላይ ለአርሱ እንድኖር እንደሚፈልግ ተረዳሁኝ።

 

ከዚህ አይነት አገልግሎት ለመውጣት እየታገልገኩኝ ባለሁበት ወቅት፣ አንድ ካሊፎርኒያ ውሰጥ ቤተ ክርስቲያን እየተከለ የነበረ ወዳጄ በትርፍ ጊዜዬ የወጣት መጋቢ ሆኜ እንዳገለግል ደውሎ ጠየቀኝ። ለመማር እና ለማደግ ጥሩ ቦታ መስሎ ታየኝ፤ ስለዚህ እኔና ክርስቲን ጓዛችንን ሸክፈን ተነሳን፤ ልክ እንደ አዲስ ሙሽራነታችን፣ አዲሱንም እምነት አሀዱ ብለን ጀመርን።

 

አገልግሎቱን እንደጀመርኩኝ እግዚአብሔር የመጨረሻ የሆነውን እንቅፋት በቆየ እምነቴ ላይ አስቀመጠ። እውነት ልክ እንደ ጸጋ ሞገድ በፍጥነት ጮሆ ፈነዳ። ይህ የሆነው የመጀመሪያ ስብከቴን፣ በዮሐ ፭÷፩-፯ (ስለ ቤተሳይዳው ፈውስ) ባለው ክፍል ላይ ስዘጋጅ ነበር። በዚህ ጊዜ ያ መጋቢው ወዳጄ የታመነ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ ሰጠኝ። ከዛ በኋላ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ የራሱን ሚና ተወጣ። እንግዲህ ክፍሉ የሚያሳየው ኢየሱስ፣ ከብዙ ሰዎች መሐል አንድ ሰው ሲፈውስ ነው፤ ሰውየው ኢየሱስ ማን እንደሆነ እንኳ አያውቅም ነበር ነገር ግን በዚያው ቅጽበት ተፈወሰ!

 

ይህ ነገር ሦስት የተለያዩ ዋጋ ያላቸውን አመለካከቶች ጥሎልኝ አለፈ። የአግዚአብሔር ፈቃድ ሁሌም እኛን ለመፈወስ አይደለም እንዴ? አይደለም፡፡ ኢየሱስ ከዛ ሁሉ ሰው መሐል ፈውሶት የነበርው አንድን ሰው ብቻ ነው። እግዚአብሔር በቂ እምነት ሲኖረን ብቻ ነው የሚፈውሰን? አይደልም፡፡ ይሄ የአልጋ ቁራኛ ኢየሱስ ማን እንደሆነ እንኳ አያውቅም ነበር (አይደለም በእርሱ ሊያምን)። ፈውስ የተቀባ ፈዋሽ፣ ልዩ ሙዚቃ፣ እና ምጽዋት አያስፈልገውም? አያስፈልገውም፡፡ ኢየሱስ ሰውየውን የፈወሰው በሌጣ ትዕዛዝ ብቻ ነው። ስለዚህ በዚህ ስግብግ እና አታላይ በሆነ አገልግሎት በመሳተፌና በሕይወቴ ስለነበረው ስሑት ትምህርትና እምነት አምርሬ አለቀስኩኝ። እግዚአብሔርንም በክርስቶስ ኢየሱስ ስለሰጠኝ ምህረትና ጸጋ አመሰገንኩ።

 

ባለቤቴ፣ ካለተናገርሽ ብዬ ችክ ማለቴን ለመጠየቅ (ለመሞገት) በመፍቀዷ እና መጋቢው ወዳጄ ከብልጽግና ወንጌል መደናገር አውጥቶ ደቀ መዝሙር ሊያደርገኝ ስለወደደ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። እግዚአብሔር የጠፉትን ነፍሳት ለመለወጥ በቅዱሳን በኩል ወንጌልን እና ደቀመዝሙርነት እንዴት አድርጎ እንደሚጠቀም ተምሬበታለውና። የአንድ ክርስቲያን ትልቁ ብቃት ለአግዚአብሔር ዝግጁ መሆን ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ ከእርሱ ጋር በእምነት ለመራመድ ሲዘጋጅ እና እውነትን በፍቅር ሲናገር ሰዎች ይለወጣሉ። እግዚአብሔርም ይከብራል። በእናንተ ታማኝነት ማን ሊድን እንደሚችል አታውቁ ይሆናል።

 

ኮስቲ ሒን ነኝ ከካሊፎርኒያ፤ 

 

ትርጉም ገዛኸኝ ዘበነ

 

http://www.christianitytoday.com/ct/2017/october/benny-hinn-costi-uncle-prosperity-preaching-testimony.html?start=1

Read 7889 times Last modified on Tuesday, 31 October 2017 11:35
Gezahegn Zebene

ገዛኸኝ ዘበነ ፤ ነዋሪነቱን አርሲ ነገሌ ያደረገና የጌታ ወንድሞች ለመባል በተጠሩት ማኅበረ ምዕመን ውስጥ ወንድም ለመሆን በጌታ ዳግም ልደትን ያገኘ ወንድም ነው። ስፋቱና ጥልቀቱ ከመታወቅ በላይ የሆነውን የጌታን ፍቅር ለመራደታ የሚተጋ እንደሆነ እና ከሁሉ ይልቅ “ወንድም” ተብሎ ቢጠራ ደስታው እንደሆነ እንዲታወቅለት ይፈልጋል።

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 131 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.