You are here: HomeNews/Eventsየሕክምና ባለሙያዎች ፈውስን በተመለከተ ለቤተ ክርስቲያን የምክር ሐሳብ ሰጡ

የሕክምና ባለሙያዎች ፈውስን በተመለከተ ለቤተ ክርስቲያን የምክር ሐሳብ ሰጡ

Published in News and Events Tuesday, 18 July 2017 12:55

መግቢያ

የክርስቲያን ሐኪሞች እና ዴንቲስቶች ማኅበር - በኢትዮጵያ፣ በአባላቱ መካከል መተናነጽን ለመፍጠር እንዲሁም ለአብያተ ክርስቲያናት እና ለአገር ጠቃሚ ጕዳዮችን ለማበርከት በሚል ዐላማ የተሰባሰቡ የወንጌላውያን ክርስቲያን ሐኪሞችን በማቀፍ ከ30 ዓመታት በፊት የተመሠረተ መንፈሳዊ ማኅበር። ማኅበሩ ከዚህ በፊት የጤና እና የሕክምና ጕዳዮችን በተመለከተ ለአብያተ ክርስቲያናት አስፈላጊውን ትምህርትና ምክር ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣ በተለይ ኤች አይ ቪ - ኤድስ የአገርም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ተግዳሮት በነበረበት ወቅት፣ የቅድመ ጋብቻ የኤች አይ ቪ ምርመራ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲተገብሩት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ይህም ድርጊት በብዙ አብያተ ክርስቲያናት እና አባላት ዘንድ ከጕዳዩ ጋር ለተያያዙ ውስብስብ ችግሮች መፍትሔን አምጥቷል። በኢትዮጵያ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በፈውስ አገልግሎት ዙሪያ ስላሉት አንዳንድ ተጨባጭ ክስተቶች የማኅበሩ አባላት በተከታታይ ከተወያዩ በኋላ፣ ለአብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮች እና ምእመናን ሁሉ ጠቃሚ ነው ያሉትን መልእክት አስተላልፈዋል።

 

ማኅበሩ በሕክምናና በሽታን በመከላከል ሙያ ሕዝባችንን የሚያገለግሉ አባላትን የያዘ የወንጌላውያን ክርስቲያኖች ማኅበር ሲሆን፣ በሽታንና ፈውስን በተመለከተ የማኅበሩ አባላት ያላቸው እምነትና በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በሚገኙ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በፈውስ ዙሪያ ስላሉት ክስተቶች ያለው ግንዛቤ እንደሚከተለው ነው፡-

 

  1. በሚታወቅም ሆነ በማይታወቅ ምክንያት በሰው ላይ የሚከሰት በሽታና ስቃይ ከመጀመሪያዎቹ ከሰው ልጆች (ከአዳም እና ሄዋን) በኀጢአት ከመውደቅ ጋር ተያይዞ እንደ መጣ ከእግዚአብሔር ቃል እንረዳለን (ዘፍ 3፥7-19)።
  2. ሰዎች ከውድቀት በኋላ በምድር ላይ በብዙ ድካምና ወዝ እንዲኖሩ እንደ ታዘዙ ሁሉ፣ የሚደርስባቸውን ችግርና በሽታም ራሳቸውንና አካባቢያቸውን በአግባብና በንጽሕና በመጠበቅ ለሕመም ከሚያጋልጡ ሁኔታዎች እንዲጠበቁ መጽሐፍ ቅዱስ ያዛል (ዘዳ 23፥12-14)።
  3. በተላላፊ ሕመም የተያዘ ሰው በሽታውን ወደ ሌላ ሰው እንዳያስተላልፍ ከሕመሙ እስኪድን ድረስ ራሱን ከሰው ለይቶ እንዲያቆይ መጽሐፍ ቅዱስ ያሰተምራል። ብሉይ ኪዳን ስለ እባጭ፣ ስለ ፈሳሽ፣ ሰለ ቆዳ በሽታ ካህኑ እንዲመረምርና እንዲያክም የመከላከል ርምጃም እንዲወስድ መመሪያ ይሰጣል (ዘሌ 13-15)።
  4. ይህን ሁሉ አልፎ በሰው ላይ ለሚከሰት ሕመም ግን እግዚአብሔር በቸርነቱና በርኅራኄው ከሕመሙ የሚድንበትን መድኃኒትና ያለ መድኃኒትም በመለኮታዊ ኀይል የሚፈወስበትን መንገድ አዘጋጅቷል። ይህም በቀደሙት የመጽሐፍ ቅዱስ አባቶችም ዘንድ ሆነ በዘመናችን ሲገልጥ ታይቷል (ኢሳ 38፥21፤ ኤር 8፥22፡ 46፥11፡ 51፥8፤ ሕዝ 47፥12፤ ቆላ 4፥14)።
  5. የማኅበሩ አባላት የተገለጠውን የእግዚአብሔር ጥበብና ማስተዋል ተምረው በሳይንሳዊ መንገድ ሰዎችን የመርዳት ተግባራቸውን የሚያከናውኑ ሲሆን፣ ይህም ተግባር ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው ኃላፊነት መሆኑን ያምናሉ።
  6. በዚህም ሳይንሳዊ ጥበብ አማካኝነት በርካታ ሰዎች ከስቃይና ከበሽታ ድነው የቀደመው ጤንነታቸው ተመልሶላቸው ሲሄዱ፣ አንዳንዶች ደግሞ መድኃኒታቸውን ያለ ማቋረጥ እየወሰዱ በተሻለ የጤንነት ሁኔታ ሲኖሩ ማየት የተለመደ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ከሳይንሱና ከሌሎችም የአቅም ውስንነቶች የተነሣ የሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ማየት የማኅበሩ አባላት በሙያቸውም ሆነ በማኅበራዊ ኑሯቸው ዙሪያ የሚያጋጥሟቸው ክስተቶች ናቸው።
  7. ይህ በእንዲህ እያለ፣ የማኅበሩ አባላት በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እንደምናነብበው ሁሉ፣ ዛሬም እግዚአብሔር የሰው አእምሮ ሊረዳው በማይችለው መለኮታዊ መንገድ ወይም በተኣምር ሰዎችን ከሕመማቸው ይፈውሳል ብለው ያምናሉ፤ ጸሎትን ያበረታታሉ፤ ራሳቸውም ለሕመምተኞች ይጸልያሉ፣ በጸሎታቸውም እግዚአብሔር ሲፈውስ አይተዋል።
  8. ይህ መለኮታዊና ተኣምራዊ ፈውስ በማንም፣ በምንም ምክንያት ሳይሆን በእግዚአብሔር ቸርነትና ለሰው ልጆች ባለው ርኅራኄ ምክንያት አምነው እርሱን ለሚለምኑት የሚሰጥ በጎ ችሮታ ነው ብለው ያምናሉ።
  9. በሕክምና ሳይንስ አማካኝነት የሚፈወሱትንም እግዚአብሔር ለሰዎች በገለጠላቸው ጥበብ የተገኘ ፈውስ ነው ብለው ያምናሉ። ይህንንም መጽሐፍ ቅዱስ የሚደግፈውና የቀደሙት የብሉይና የአዲስ ኪዳን አባቶችም የተቀበሉትና የተለማመዱት መሆኑን አባላቱ ያምናሉ።
  10. የማኅበሩ አባላት በጌታ በኢየሱስም ሆነ በሐዋርያት አገልግሎት ተፈውሳችኋል የተባሉ ሕመምተኞች ሁሉ መፈወሳቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ይረዳሉ (ማቴ 9፥32፡ 17፥14-18፤ ማር 2፥3-7፡ 5፥5-31፤ ሉቃ 4፥33-39፡ 5፥12-14፡ 7፥14-15፡ 9፥42፡ 13፥10-13፡ 14፥1-4፡ 17፥11-16፤ ዮሐ 11፥43-44፤ ሐሥ 3፥16)።
  11. ለፈውስ ከተጸለየላቸው ሰዎች መካከል እኛ በማይገባንና እግዚአብሔር በሚያውቀው ምክንያት ሳይፈወሱ የቀሩ ሊኖሩ እንደሚችሉ እናምናለን። ስለዚህ ያልተፈወሱትን ሰዎች ሁሉንም ከእምነት ማነስ ነው ብሎ መፈረጅ ተገቢ እንዳልሆነ እናምናለን (2ቆሮ 12፥8-10፤ 2ጢሞ 4፥20)።
  12. አሁን በአገራችን በሚታየው ሁኔታ በትክክል በጸሎት የተፈወሱ መኖራቸውን የሚመሰክሩት ሐቅ ቢሆንም፣ በተቃራኒው ደግሞ ተፈውሳችኋል የተባሉ ሁሉ እንዳልተፈወሱ፣ አንዳንዶችም እንደተባባሰባቸው፣ አንዳንዶችም እንደ ሞቱ፣ አንዳንዶችም ሳይፈወሱ ተፈውሳችኋልና መድኃኒታችሁን ጣሉ እንደ ተባሉ አባሎቹ በሥራቸው ምክንያት ካጋጠማቸውና ከሌሎችም ሰዎች ባገኙት ምስክርነት መረዳት ችለዋል። ይህ ደግሞ ለሰዎች ጉዳትን ያስከተለ፣ ለቤተ ክርስቲያን ነቀፋን ያመጣ፣ ሲቀጥልም በሕግ ተጠያቂነትን ሊያስከትል የሚችል ተግባር መሆኑን ማኅበሩ ይረዳል።
  13. ተፈውሳችኋል፣ ተብለው ሳይፈወሱ የቀሩ ወይም ተፈውሰናል ብለው በማመን መድኃኒታቸውን አቋርጠው ጉዳት የደረሰባቸው፣ ሲከፋም የሞቱ ሰዎች በአብዛኛው የውስጥ ደዌ ወይም የአእምሮ ሕመም ያለባቸውና የነበራቸው መሆናቸውን የማኅበሩ አባላት ይረዳሉ።

 

ስለዚህ የሕዝባችንን ጤንነት ከጉዳት መጠበቅ የሙያ ግዴታችን፣ የቤተ ክርስቲያንን እውነተኛነትና በኅብረተ ሰቡ ዘንድ ተአማኒነትዋን ለመጠበቅ አስተዋጽዖ ማድረግ ደግሞ ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው ብለን እኛ የማኅበሩ አባላት ስለምናምን እና ጤና ነክ በሆኑ ጕዳዮች ዙሪያ ቤተ ክርስቲያንን ለማማከር ማኅበራችን ከተቋቋመባቸው ዐላማዎች አንዱ በመሆኑ፣ ጤንነትንና መለኮታዊ ፈውስን በተመለከተ ለወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያናት የሚከተለውን መልእክት/ምክር ማስተላለፍ እንወዳለን።

 

  1. ሰውነታችን የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የሚናገረው (1ቆሮ 3፥16-17፡ 6፥19-20) ጕዳይ ስለ ሆነ ሰውነታችንን በጥንቃቄ መጠበቅና መንከባከብ እንደሚያስፈልግ፣ መነሻቸው ከሚታወቁ የበሽታ ዐይነቶችም መከላከል እንደሚያስፈልግ ቤተ ክርስቲያን ማስተማር ይኖርባታል ብለን እናምናለን። ይህም የራስንና የአካባቢን ንጽሕና መጠበቅን፣ ከልዩ ልዩ ሱስ የጸዳ ሕይወት መኖርን፣ አመጋገብን ማስተካከል፣ የአካል እንቅስቃሴን ማዘውተር ወዘተ. የሚያጠቃልል ይሆናል። ስለዚህ ጕዳይ አጥብቀው የሚያስተምሩ አማኞች ላይ በአሜሪካን አገር የተደረጉ ጥናቶች አባሎቻቸው ከሌላው ኅብረተ ሰብ በተሻለ ጤንነት ሕይወታቸውን እንደሚመሩና ረጅም ዕድሜ እንደሚኖሩ አሳይተዋል። ይህም ለጠቃሚነቱ ማሳያ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል ብለን እናምናለን።

  2. በሚታወቅም ሆነ በማይታወቅ ምክንያት ሰዎች ሕመም በሚያጋጥማቸው ጊዜ የእግዚአብሔርን ፈውስ በእምነት እንዲጠይቁ ማስተማሩ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ የግድ በዚህ መንገድ ብቻ ነው ሰው ሁሉ መፈወስ ያለበት በማለት ዘመናዊ ሕክምናን መፈለግን ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚያጣላ ድርጊት አድርጎ ማስተማር እንዳይኖር እንመክራለን።

  3. አንዳንድ የሕመም ዐይነቶች፣ በተለይም የውስጥ በሽታዎች ለምሳሌ፡- የጨጓራ፣ የጉበት፣ የሳምባ፣ የኩላሊት፣ የአእምሮ ወዘተ. የመሳሰሉት ፈውሳቸው በጊዜ ሂደት ካልታየ በስተቀር ርግጠኛ መሆን ስለሚያስቸግር፣ ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች ከተጸለየላቸው በኋላ ተፈውሳችኋል ተብለው ወዲያውኑ ለምስክርነት እንዳይቀርቡ እንመክራለን። ምክንያቱም በአብዛኛው ስሕትት እየታየባቸው ያሉ ሕመሞችና የፈውስ መልእክቶች ከእነዚህ ዐይነት በሸታዎች ጋር የተገናኙ በመሆናቸው ማረጋገጡን ተገቢ ያደርገዋል።
  4. በግልጽ ከማይታዩ በሽታዎች ተፈውሰዋል የተባሉ ሰዎች ሁሉ ፈውሳቸው እውነተኛ ለመሆኑ በሕክምና ምርመራ ቢረጋገጥ ብዙ ጥቆሞች ስላሉት ተፈውሰሃል/ተፈውሰሻል የሚል መልእክት የመጣላቸው ሰዎች ሁሉ ምርመራ እንዲያደርጉ ቤተ ክርስቲያን አጥብቃ እንድታስተምር እንመክራለን። ምናልባት ይህ ምክር በጣም ግልጽና ውጫዊ የሆነ በሽታ ስለነበረባቸው ሰዎች፣ ለምሳሌ በግልጽ ስለሚታይ የአካል ጉዳት፣ የማየት፣ የመስማት ወዘተ. ዐይነት ችግሮች ፈውሱ በግልጽ ስለሚታወቅ እውነት ለመሆኑ ልዩ ማረጋገጫ ላያስፈልጋቸው ይችል ይሆናል።

 

ሆኖም ግን የሕክምና ምርመራ ማድረጉ ብዙ ጥቅሞች አሉት ብለን እናምናለን። እነዚህም፡-

 

  • ተፈውሰሃል ለተባለው ሰው የበለጠ ርግጠኝነትን ስለሚሰጠው፤

  • በሽታውን መርምሮ ላገኘውና ላረጋገጠው የሕክምና ባለ ሙያ ስለ እግዚአብሔር
    ፈዋሽነት ምስክር ስለሚሆነው፤

  • የፈውስ መልእክቱን ያመጣው ግለ ሰብ እውነተኛ የእግዚአብሔር መልእክተኛ መሆኑን
    ለማረጋገጥ፤ እውነተኛ ካልሆነ ከስሕተቱ እንዲታረም ለማስተማር/ለመምከር፣
    እውነተኛውን ደግሞ ለማበረታታትና ለመደገፍ ስለሚረዳ፤

  • የቤተ ክርስቲያንን ተአማኒነት ለመጠበቅና አባላትን ከስሕተት ለማዳን ስለሚጠቅም
    ነው።
  1. በምርመራ ፈውስን ማረጋገጥ እግዚአብሔርን እንዳለማመን ወይም እርሱን እንደ መፈታተን አድርገው የሚወስዱና ይህ እንዳይሆን የሚመክሩ ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን። ይህንን ምክር በእኛ በኩል የተሳሳተ ምክር ነው እንላለን። ይህንንም የምንልበት ምክንያት ምርመራ የሚደረገው እግዚአብሔርን በመጠራጠር ሳይሆን፣ የመልእክቱን እውነተኛነት ለማረጋገጥ ነው። ይህ ደግሞ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ መርምሩ፣ ፈትኑ፤ ብሎ ከሚመክረን ከመጽሐፍ ቃል ጋር ይስማማል ብለን እናምናለን። የእግዚአብሔር ሥራ/ፈውስ ማንኛውንም ዐይነት ምርመራና ጥያቄ የሚያልፍ፣ ከሰው አእምሮ በላይ የሆነ ነው እንጂ ምርመራን ወይም ጥያቄን የሚፈራና የሚደነግጥ አይደለም (1ዮሐ 4፥1፤ 1ተሰ 5፥19-22)።

  2. በዘመኑ ባለው የሕክምና ሳይንስ መስፈርት መሠረት፣ ምርመራ አካሂዶ በሽታው አለብህ/አለብሽ ብሎ የተናገረው ባለ ሙያ በተመሳሳይ መልኩ ምርመራ አድርጎ የለብህም/የለብሽም ቢል ከሥነ ምግባርም፣ ከሕግም አንጻር ትክክል ስለሚሆን ይህን ማድረግ የሚመከር መሆኑን እንደገና እየገለጽን መድኃኒት አቁሙ ብሎ ሕመምተኛውን መምከርንም ለባለ ሙያ መተው አስፈላጊ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን አምና ለአባሎቿ እንድታስተምር እንመክራለን።

  3. የዚህ መልእክት ወይም ምክር ዐላማ በማንም ላይ ትችትን ለመሰንዘር ሳይሆን፣ እንደ እግዚአብሔር ቃል የሆኑ ልምምዶችን ለማደፋፈር እንዲሁም በሙያችን ዙሪያ ካጋጠሙንና በቤተ ክርስቲያን እየተከሰቱ ስላሉ ስሕተቶች ጥቆማን ለመስጠትና ለመፍትሔውም የሚሆኑ ሐሳቦችን ለመሰንዘር ነው። ስለሆነም በዚህ ርእሰ ጕዳይ ዙሪያ ጥያቄዎች ለማንሣት፣ ለመወያየት፣ ለመመካከር ፍላጎት ላላቸው ቤተ ክርስቲያኖች፣ ድርጅቶች፣ ቡድኖችም ሆነ ግለ ሰቦች ሁሉ ይህን ለማድረግ ማኅበራችን ዝግጁ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን፤ ይህም እንዲሆን እናደፋፍራለን።

  4. በዚህ አጋጣሚ ቤተ ክርስቲያን አባሎቿን፣ ስለ ግል መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት ንጽሕና፣ ስለ ማኅበራዊ ተሳትፎ፣ ስለ ቃልና ተግባራዊ ምስክርነት እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በኋለኛው ዘመን ሊመጣ ስላለው የመንፈስ የስሕተት አሠራር በማስተማር ሕዝቧን ከጉዳት ለመጠበቅ ሁለንተናዊ ኀለፊነትዋን ለመወጣት በምታደርገው ጥረት ማኅበራችን ከጎኗ የሚቆም መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።


የክርስቲያን ሐኪሞችና ዴንቲስቶች ማሕበር - በኢትዮጵያ
አድራሻ፡- ስልክ 0910133019 ኢሜይል፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Read 6673 times Last modified on Tuesday, 18 July 2017 13:15

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 91 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.