You are here: HomeNews/Eventsየኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣በአስተምህሮ ዝንፍት፣ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆኑ ልምምዶችና በሞራል ውድቀት ላይ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣በአስተምህሮ ዝንፍት፣ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆኑ ልምምዶችና በሞራል ውድቀት ላይ የተሰጠ መግለጫ

Published in News and Events Saturday, 08 April 2017 11:20


መግቢያ

እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች አገራችን ኢትዮጵያ ከመጀሪያዎቹ መቶ ዓመታት ጀምሮ የወንጌልን እውነት የተቀበለች አገር መሆኗን እናውቃለን፡፡ በተለይም ደግሞ፣ ካለፈው አንድ ምእተ ዓመት ገደማ ጀምሮ እግዚአብሔር በምድራችን ያደረገውን ድንቅ የወንጌል እንቅስቃሴ እናደንቃለን፡፡ በዚህም እንቅስቃሴ ሚሊዮኖች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ፈልሰዋል፤ የብዙዎች ሕይወት ተቀይሯል፤ እጅግ ብዙዎች ከተለያዩ እስራቶች ተፈትተዋል፤ ከአምላካችንም የምሕረትና የርኅራኄ እጅ ብዙዎች ፈውስን ተቀብለዋል፡፡ ዛሬም፣ እግዚአብሔር አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ብዙዎችን ወደ መንግሥቱ እያፈለሰ፣ ድንቆችንና ታምራቶችን እየሠራ ብዙዎችን ከእስራት እየፈታ እንደሆነ ምስክሮች ነን፡፡ ለዚህ ሁሉ ክብሩን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንሰጣለን!


እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች፣ “ወንጌላውያን” ያሰኙን፣ መሠረታቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑና በርቱእ ክርስትና ውስጥ ተቀባይነት ያላቸው አስተምህሮዎች አሉን፡፡ ከሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርእቱኣን ታሪካዊ የክርስትና እምነት መግለጫዎች ማለትም የሐዋርያት፣ አትናቴዎስ፣ ኒቂያ እና ኬልቄዶን ጋር ተያይዞ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የእምነት አቋም እንቀበላለን፡፡

 
በእስትንፋስ መለኮት የተጻፉትን የ66ቱን የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ስሕተት አልባነት፣ ተኣማኒነት፣ ብቁነትና እና በእምነትና በተግባር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በሥርዐተ አምልኮ ሁሉ ላይ ያላቸውን የበላይ ባለ ሥልጣንነትና ዳኝነት፣ ራሱን በሦስትነት የገለጠ አንድ እውነተኛ አምላከ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ መኖሩን፣ የሕያው እግዚአብሔር አንድያ ልጀ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን፣ የእኛ ምትክ ሆኖ ለኀጢአት ስርየት በመስቀል ላይ መሞቱን ከሞትም በአካል መነሣቱን፣ በዓለም ፍጻሜም ዳግም የሚመለስ መሆኑን አካላዊ መንፈስ የሆነው መንፈስ ቅዱስ፣ ከአብና ከወልድ ጋር የተካከለ አምላክ መሆኑንና አማኞችን በኀይል በመሙላትና እንደፈቃዱም የጸጋ ሥጦታዎችን በማደል ቤተ ክርስቲያንን የሚያንጽና ለአገልግሎት የሚያሰማራ መሆኑን፣ ድነት በእግዚአብሔር ጸጋ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ የሚገኝ መሆኑን፣ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም የኀጢአት ስርየት ያገኙ እውነተኛ አማኞችን ሁሉ የምትይዝ አንዲት የክርስቶስ አካልና የእምነት ማኅበረ ሰብ መሆኗን እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ለስብከተ ወንጌል ጥሪና ተግባር ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን እናምናለን፡፡

 

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት 32ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በአስተምህሮ መዛነፎች ላይ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ልምምዶች እና የሞራል ውድቀት ጕዳዮች ላይ የቀረቡትን የጥናት ወረቀቶች ካደመጥንና ከተወያየን በኋላ፣ ጕዳዩ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ከመገንዘባችን በላይ፣ አፋጣኝ መፍትሔ ካልተሰጠው የክርስትናን መሠረታዊ ይዘት የሚያፋልስ፣ የመንፈስ አንድናታችንን የሚያናጋ፣ የወንጌልን ግስጋሴ የሚገታ ትልቅ አደጋ እንደተጋረጠብን ታይቶናል፡፡ በመሆኑም፣ የሚከተለውን ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

 

  1. እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፣ “የእምነት ቃል እንቅስቃሴ” ተብሎ በሚጠራው የስሕተት ትምህርት ላይ ያለንን ጽኑ ተቃውሞ እንገልጻለን፤ አስተምህሮው “ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ይኖራል” ማለቱን፣ “እኛ እና አብ አንድን ነን” ማለቱን፣ “እኛ እና ክርስቶስ አንድን ነን” ማለቱን፣ “እኛ ትንንሽ አማልክት ነን” ማለቱን፣ “ክርስቶስ ሰይጥኗል” ማለቱን፣ “እኛ ካልፈቀድንለት በስተቀር እግዚአብሔር በምድር ላይ መሥራት አይችልም፤ ሕገ ወጥ ይሆናል” ማለቱን፣ “የእኛ እምነት እንደ እግዚአብሔር ያለ እምነት ነው” ማለቱን፣ “በሥጋ የሚሠራ ኃጢአት ችግር የለውም” ማለቱን፣ “የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ለኃጢአት ስርየት በቂ አይደለም” ማለቱን እና ሌሎች መሰል ትምህርቶቹን አጥብቀን እየተቃወምን፣ እነዚህ አስተምህሯዊ አቋሞች በእግዚአብሔር ቃል ላይ ከተመሠረተው የወንጌላውያን ክርስትና አስተምህሮ ጋር ፍጹም የሚቃረንና የማይወክለን መሆኑን እንገልጻለን፤


  2. እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፣ “የብልጽግና ወንጌል” ተብሎ በሚጠራው የኑፋቄ/የስሕተት/ ትምህርት ላይ ያለንን ጽኑ ተቃውሞ እንገልጻለን፤ አስተምህሮው፣ “አማኞች ፍጹም ሊታመሙ አይችሉም” ማለቱን፣ “አማኞች ፍጹም ሊደኸዩ አይችሉም” ማለቱን፣ “ሰዎች የሚታመሙትም ሆነ የሚደኸዩት ከእምነት ዕጦት የተነሣ ነው” ማለቱን፣ “ከአንደበታችን የሚወጣው ቃል ልክ እንደ እግዚአብሔር ቃል የመፍጠርና የማድረግ ጉልበት አለው” ማለቱን እና “የክርስቶስን መስቀል ምሳሌያዊ ጥሪ አንቀበልም” ማለቱን እና መሰል ትምህርቶቹን አጥብቀን እየተቃወምን፣ እነዚህ አስተምህሯዊ አቋሞች በእግዚአብሔር ቃል ላይ በተመሠረተው የወንጌላውያን አስተምህሮ ጋር ፍጹም የሚቃረንና እኛን የማይወክለን መሆኑን እንገልጻለን፤


  3. እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ፍጹም ባለሥልጣነት በቃልም ሆነ በተግባር የማይቀበሉትን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በሙላት የማይቀበሉትን፣ የክርስቶስን ፍጹም ሰውነት እና መለኮትነት በማይነጣጠል፣ በማይከፋፈል እና በማይለዋወጥ አንድንት መኖሩን የሚክዱና የሚበራርዙ ትምህርቶችን፣ በሥጦታዎች ላይ መበላለጥን፣ የሎሌነትን መንፈስ የሚጻረር የግለ ሰብ ግነትንና ማእከልነት እንዲሁም ጤናማ ያልሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎምን የሚያራምዱትን እንቃወማለን፤ የማይወክሉን መሆኑንም እንገልጻለን፤


  4. እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፣ በዚህ የአቋም መግለጫ መግቢያ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች በዚህም ዘመን መሥራታቸውን የምናምንና የምንለማመድ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፤ በአንጻሩ በመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ስም የሚደረጉ ማጭበርበሮችን፣ ሥጦታዎቹን የገንዘብ ማግኛ መንገድ ማድረግን፣ የተለያዩ ቁሳቁሶችን፣ ማለትም እንደ ዘይት፣ ጨው፣ ውሃ፣ ጨርቅ፣ አፈር፣ ወዘተ. “የተጸለየባቸው ናቸው” በሚል ለሽያጭ ማቅረብን፣ ለጸሎት የሚመጣ ጥያቄን በገንዘብ መደራደርን እና የመሳሰሉትን ማጭበርበሮች አጥብቀን እየተቃወምን፣ እነዚህ ልምምዶች ከእኛ ከወንጌላውያን ክርስትና አማኞች ጋር ፍጹሞ የሚቃረኑና የማይወክለን መሆኑን እንገልጻለን፤ በተጨማሪም፣ በሃይማኖት ስም የሚደረጉ ማናቸውንም ዐይነት ማጭበርበሮች በሚመለከት ለሚነሡ ሕጋዊ ክሶች የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ምንም ዐይነት ሽፋንም ሆነ ከለላ የማይሰጡ መሆኑን እናሳውቃለን፤


  5. እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝ መሆኑን አምኖ የተቀበለና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነ አማኝ ሁሉ፣ የጽድቅና የቅድስና ሕይወትን የሚለማመድ መሆኑን በጽኑ እናምናለን፤ በአንጻሩ ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርና ሞራል ፍጹም በተቃራኒ የሚደረግ የኃጢአት ልምምድን፣ ማለትም አመንዝራነት፣ ግብረ ሰዶማዊነት፣ የቅድመ ጋብቻ ሩካቤ ሥጋ፣ ፍቺና ተደጋጋሚ ጋብቻን፣ ታማኝነት ማጉደልን፣ ወዘተ. ከእኛ የወንጌላውያን ክርስትና አማኞች ጋር ፍጹም የሚቃረንና የምናወግዘው መሆኑን እንገልጻለን፤


  6. እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ከውጪ አገር እየመጡ የተለያዩ የኑፋቄ ትምህርት የሚያስተምሩ፣ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ዜጎች መኖራቸውን ተገንዝበናል፤ በመሆኑም፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ከውጪ አገር ለሚመጡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጤናማነታቸው ሳይረጋገጥ መድረኮቻችንን አሳልፈን እንዳንሰጥ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ተገንዝበናል፤ በተያያዘም፣ ከላይ በተገለጹት የኑፋቄ ትምህርቶች፣ ባዕዳን ልምምዶችና እና ሞራል ውድቀቶች ውስጥ ያሉ ግለ ሰቦችን የሚያበረታቱና እውቅና የሚሰጡ አገልጋዮች ከዚህ ተግባራቸው እንዲታቀቡ እናሳስባለን፤


  7. እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በርካታ የኑፋቄና የስሕተት ትምህርቶች፣ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ልምምዶችና ሞራላዊ መሠረቶችን የሚያናጉ ሐሳቦች ከሚተላለፉባቸው መንገዶች ዋነኞቹ የብዙኀን መገናኛዎች (የቴሌቪዥን፣ የሬዲዮ፣ የኅትመት እና የማኅበራዊ ሚዲያዎች) መሆናቸውን ተገንዝበናል፤ በመሆኑም፣ የትኞቹ የብዙኅን መገናኛዎች በዚህ ችግር ውስጥ እንዳሉ በመለየት አገልጋዮችና ምእመናን እንዲጠበቁ ማድረግ እንዳለብን አጥብቀን እናምናለን፤ በተጨማሪም፣ ጤነኛው ትምህርት የሚተላለፍባቸው የብዙኀን መገናኛዎችን ማበረታታና የወንጌላውያንን ድምፅ የሚያስተጋቡ ሌሎች የብዙኀን መገናኛዎችን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ለማድረግ ቃል እንገባለን፤


  8. እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፣ ከላይ በተጠቀሱት የተሳሳቱ የአስተምህሮ፣ የልምምድና የሞራል መንገድ ውስጥ ያሉ ቤተ እምነቶች፣ መገናኛ ብዙኀን እንዲሁም ግለ ሰቦች፣ ካሉበት የተሳሳተ አካሄድ እንዲመለሱ በራችንን ክፍት አድርገን በክርስቲያናዊ ፍቅር ጥሪ እናደርጋለን፤ ነገር ግን ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች በማይሆኑትና በስሕተት መንገዳቸው ለመቀጠል በፈቀዱት ላይ ተገቢው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርምጃ እንዲወሰድ፣ ይህንንም የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሥራ አመራር ቦርድና የኅብረቱ ፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት በጋራ እንዲያስፈጽሙት ሙሉ ኀላፊነት እንሰጣለን፤


  9. እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፣ በምድራችን ላይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን አሁን ለደረሰችበት ችግር እኛም መሪዎቿ ተጠያቂዎች መሆናችንን እንቀበላለን፤ ይህም ሲባል በቂ እና ተገቢ ትምህርት አለመስጠታችን፣ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎችን በተገቢው መንገድ አለማበረታታታችን፣ መድረካችንን ለሐሰት ትምህርቶችና ልምምዶች ክፍት ማድረጋችን እንዲሁም ስሕተቶች ሲፈጠሩ ፈጣን የእርምት ርምጃ አለመውሰዳችን፣ በጸጋ ሥጦታዎች መካከል ማበላለጣችን፣ በዚህም እግዚአብሔርን ማሳዘናችንን እየተገነዘብን፣ ባለማወቅም ሆነ በአሠራር ጉድለት የተበደሉ ወይም የተጎዱ ወንድሞችና እኅቶች እንደሚኖሩ በመረዳት ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ምሕረት እንጠይቃለን፤ ከዚህም የተነሣ የተጎዱ ምእመናንን ይቅርታ እንጠይቃለን፤ ቤተ ክርስቲያን ከገባችበት አሳሳቢ ችግር እንድትወጣ ተገቢውን የንስሓና የምልጃ ጸሎት በየቤተ እምነቶቻችን እናደርጋለን፤ እውነተኛውን ትምህርት በትጋት የማስተማርና ደቀ መዝሙር የማድረግ ኃላፊነታችንን እንወጣለን፤
    በየቤተ ክርስቲያናቱ ያሉ ምእመናንም በዚህ ረገድ ለበደሉት ማናቸውም በደል ሁሉ የጌታን ምሕረት እንለምናለን፡፡


  10. እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፣ ዛሬ መጋቢት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ያወጣነው የአቋም መግለጫም ሆነ የኅብረቱ ጽ/ቤት ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወደ ፊት የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች ለመተግበር ቃል እየገባን፣ ይህንንም ባለን የቤተ ክርስቲያን መዋቅር መሠረት ለማስጸፈም፣ በየክልሉ ካሉ የወንጌላውያን አብያት ክርስቲያናት አደረጃጀቶች ጋር በአንድነት በመሥራት መንጋዎቻችንን የመጠበቅ ኃላፊነታችንን እንደምንወጣ እንገልጻለን፤
    ይህ መግለጫ እንደየአስፈላጊነቱ ተገቢ ለሆኑ ተቋማት እና ድርጅቶች እንዲደርስ ጽ/ቤቱ እንዲሠራ እናሳስባለን፡፡


    እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑን ይጠብቅ፤ አገራችንንም ይባርክ!
    መጋቢት 22 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

 

Read 8019 times Last modified on Wednesday, 12 April 2017 10:15

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 115 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.