You are here: Home

የልጆቾ ወላጅ ማነው?

Written by  Saturday, 12 July 2014 00:00
የልጆቾ ወላጅ ማነው? Photo: BEKI Square

ርእሴን ያነበበ ሰው፣ “ወዴት ወዴት ነው?”  ሊል ይችላል ፡፡ ቀዩኝ! ወዴትም አይደለም፡፡ አሊያም፣ “ስያሜው ራሱ የሚጋጭ ነው፤” በሚል በሰላ ሂስ መጣጥፌን ሊጀመርው ይመርጥም ይሆናል ፡፡ ግድ የለም ጥቂት ታግሳችሁ ስሙኝ፡፡ በአካል ወላጆች ፊት ካለመሆኔ የተነሳም፣ “የልጆቼ ወላጅማ እኔ ነኝ፤ ምስክሩም የወገቤ ፍሬ  መሆናቸው ነው፤” በሚል  ንግግሬን እንዳልቀጥል  ድፍረት ሊያሳጣኝ  የሚያስችል ግልምጫን  ከመቅመስ ሳልተርፍም የቀረው ይመስለኛል ፡፡ የምጠይቀው የወላጅነት ምስክር በዲኤንኤ የተካፈልነውን ክሮሞዞም ቢሆን ኖሮ  እንቆቅልሹ በላብራቶሪ ናሙና ብቻ የሚፈታም  በሆነ ነበር፡፡ መልሱንም ለመሻት ለዲኤንኤ ምርመራ ናሙናውን ባህር አሻግረን በላክነው ! ያ ቢሆንማ በመውለድ ህይወት ካካፈሉን ውጭ ሌላ ወላጆች ባልኖሩን ነበር፡፡ በህይወታችን አሻራ የተውና እንደ ልጅ የሚቆጥሩን እኛም እንደ ወላጅ የምናያቸው መኖራቸው ደግሞ ሀቅ  ነው፡፡  በእውነት፣ በህይወታችን ውስጥ ከወላጆቻችን ሌላ ወላጆች የሉንም? እንዴታ! በርእሴ ውስጥ ያነሳውት ወላጅነት ግን  ከዘር ፍሬያችን የዘለለ መልክን ለልጆቻችን እንካችሁ ከማለት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ 

  1. ወላጃቸው ማነው?

በቀደምት ጊዜያት፣ በልጆች ውስጥ ለሚታየው መልካምም ሆነ አልባሌ ባህሪ፣ ዋነኛ ተጠያቂም ወይም ተወዳሽ ተደርገው ይወሰዱ የነበሩት ወላጆቻቸው ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በልጆች ህይወት ውስጥ ለሚታየው በጎ ተጽእኖ ሆነ  መልካም ምሳሌ መታጣት ተመስጋኝም (2ኛ. ጢሞ 1፡5) እንዲሁም  ተወቃሾቹም(1ኛ ነገስት 1፡5-6) ወላጆች ተደርገውም ተወስደዋል ፡፡ እነዚህን ውድ ቀናት ግን ልብ ሳንላቸው ብዙዎቻችን እየተሰናበትናቸው መሆኑ አይካድም፡፡ ዛሬ ዛሬ፣  ወላጆችና ልጆች በጋራ አብረው የሚያሳልፉዋቸው ሰአቶች እየቀነሱ ከመምጣታቸው አንጻር፣ ልጆችን በመቅረጽ ሂደት ወላጆች ያላቸው ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው ማለትም ያስደፍራል፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ ከወላጆች ጋር ከዚህ ቀደም ይጠፋ የነበረው ጊዜ በማን ተተካ ብሎ መጠየቅም የአባት መሆኑ አይቀሬ ነው ፡፡

 

ይህንን በጥናት በተደገፈ መልኩ መመለስ የሚያስችል መረጃ በሀገራችን ባይገኝም በየቤታችንና፣ በጎሬቤቶቻችን፣ ብሎም በየመንገዱ ከምናየው ነገር በመነሳት አካሄዳች ከምእራቡ አለም ቅኝት ብዙ የተለየ አይደለም የሚል መደምደሚያ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉ በርካታ ምልከቶች አሉ፡፡ በሃገራችንሳ ከተሜ ታዳጊ ወጣቶች ዘንድም ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ያለው ዝምድና ይበልጥ እየጠበቀ ሌሎች ትስስሮች ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችላ እየተባሉ እየመጡ ነው፡፡ ታዳጊ ወጣቶች ቤት እንደገቡ ወይም መንገድ ላይ ስንመለከታቸው አይኖቻቸውንና ጆሮዎቻቸውን በበላይነት የሚቆጣጠሩት መገኛኛ ብዙሃን ናቸው ማለት ያስችላል፡፡  አይኖቻውን የያዙት በተለያየ መልክ የቀረቡ ስክሪኖች ሲሆኑም ጆሮዎቻቸውም ደግሞ ከየስፒከሮች በሚወጡ ድምጾች ወይም በጆሮዋቻቸው ላይ በተሰኩ ማዳመጫዎች መሸፈናቸውን መመልከት ይቻላል፡፡ 

 

ልጆችን በእርግጥ የምንቀሰቅሳቸው ከእንቅልፍ ብቻ ሳይሆን ከእነዚህ የመገናኛ ብዙሃን መሆኑን ለመረዳት፣ “ በቃህ፣ አሁን አስቀምጠውና አጥና፣ ብላ…ወ.ዘ.ተ” ያልንባቸውን ሳይሆን ያላልንባቸውን ቀኖች መቁጠር ሳይቀለን አይቀርም፡፡ ቀን ከሌት ያለማንም ከልካይ በብቸኝነት የሚጋቱዋቸው እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን፣ “ምን እየመገቡ?”፣ “ምናቸውን እያወፈሩ?”፣ “ደግሞም ምንንስ እያስቀሩ?” “ምናቸውን እያቀጨጩ?” ይሆን ብሎ ማሰብ በእርግጥ ከዘመን ወደ ኋላ መቅረት ሳይሆን ዘመንን መቅደም መሆኑን ግን ብዙ ወላጆች ልብ ያሉት አይመስሉም፡፡ አንዳንድ ወላጆች እንደውም ቴክኖሎጂ በየእለቱ በትትርናው እንካችሁ የሚለውን በማቅረብ ተወዳጅ ወላጅ ለመሆን የሚጥሩ እንዲሁም ከመሰል ወዳጆቻቸው ጋር የሚወዳደሩም እንዳሉ ያስተዋልኩባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ ወዳጆቼ፣ ቤተሰብ ልጆችን ጨምሮ ከሌላች ጋር የምንወዳደርባቸው ቦታዎች አይደሉም፡፡ ዋጋቸውም ሌሎች ስለ እነርሱ ምን አሉ? በሚለውም ላይ አይመሰረትም፡፡

 

ልጆቾን ለነዚህ መገናኛ ብዙሃን ሲያስረክቡ ታዲያ የሚመጥናቸውን እየመጠኑ የሚሰጡዋቸው ከመሰሎት ተሳስተዋል፡፡ መገናኛ ብዙሃኑ እንደ ስማቸው ብዙሃኑን በማሰብ ስለሚተነፍሱ፣ በቁጥጥር ካልተደመጡና ካልተመለከቱ ላልታሰበ አድማጭ ያልታሰበ ነገር ሊደርስ መቻሉ ሊዘነጋ አያስፈልግም፡፡ ብዙ ወላጆች ግን “ መሰረተ ሚዲያ” የላቸውም፡፡ መሰረተ ሚዲያ የሚለውን ቃል የቀመርኩት መሰረተ ትምህት ከሚለው ቃል በመነሳት ሲሆን የሚያመለከትውም ሚዲያን አስመልክቶ በቂ ግንዛቤ መኖርን ነው፡፡ መሰረተ ሚዲያ ያላቸው ወላጆች ሚዲያ በምን መለኩ እኛን፣ ማህበረሰብን እንዲሁም ደግሞ ባህላችን ላይ ተጽእኖ እንደሚያደርግ ግንዛቤ ያላቸው ወላጆች ናቸው፡፡ እንዲህ አይነት ወላጆች ደግሞ በተለያየ መልኩ በሚዲያ የሚቀርቡ መልእክቶች ማግኘት፣ መተንተን፣ እንዲሁም መገምገም የሚችሉ ናቸው፡፡ እንዲህ አይነት ግንዛቤ ያላቸው ወላጆችም ሆነ ልጆች ከሚዲያጋ ጋር ያላቸው ግንኙነት በንቃት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ስለዚህም የሚሰሙትን እንዲሁም የሚመለከቱትን ነገሮች ልባቸውንን እና ስሜታቸው በመከተል ብቻ ሳይሆን አመክንዬንም በመጨረም የሚገመግሙት ይሆናል፡፡ መሰረተ ሚዲያ የቀመሱ ወላጆች ደግሞ መጠኑን በመወሰን ፣ በውይይትና በንቁ ተሳታፊነት የመገነኛ ብዙሀን አካል ይሆናሉ፡፡

 

ከዚህም የተነሳ ልጆች የፈለጉትን ያህል ያለ ከልካይ ቀኑን ሙሉ የፈለጉትን መገናኛ ብዙሀን እንዲኮመኩሙ አይፈቅዱም ይልቁኑ ነገርን መመጠን እንዲችሉ ያግዙዋቸዋል፡፡ ምን አይነቶችን መመልከት እንዳለባቸው በመወሰን ሂደት ከልጆቻቸው ጋር በንቃት ይሳተፋሉ፡፡ ከልጆቻቸው ጋርም የሚያደምጡዋቸውን እና የሚያያቸውን ነገሮች ይሳተፋሉ፡፡ በሂደቱም እውነታ የለቁቁ ነገሮች በሚቀርቡበት ጊዜም እውነታውን መሰረት በማድረግ ከልጆቻቸው ጋር ይወያያሉ እድሉን በመፍጠርና ሲመቻችም ደግሞ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በነገረ ጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሀሳብ ያሳውቃሉ ፣ ሂስም ይሰጣሉ፡፡ ልጆች የተገነዙዋቸውን ነገሮች ይወያያሉ፣ ያልሆኑ ነገሮች በሚነገሩበት ጊዜም ምንም መገናኛ ብዙሃኑ ሰምቶ መልስ የማይሰጥ ቢሆንም ይመልሱለታል፡፡

 

2010 ኒዎርክ ታይምስ በተሰኘ መጽሔት ገጽ ላይ ልጆች ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ያላቸውን ቁርኝት የሚገልጽ አስገራሚ ጽሁፍን ይዞ ብቅ ብሎ ነበር፡፡ ለርእሰ ጉዳዩም የተሰጠው ስያሜ ፣ “ልጆቾ ከእንቅልፍ ነቅተው ከሆነ ምናልባትም ኢንተርኔት ላይ ተጥደዋል፡፡” የሚል ነው፡፡ምናልባት ይህ አባባል የሀገራችንን በርካታ ከተሜ ወጣቶች ሳይገልጻቸውም የቀረም አይመስለኝም፡፡ ብዙ ልጆች በተሸፋፈኑበት ብርድ ልብስ ስር ያለው ዝምታቸው የመተኛታቸው ምልክት ሳይሆን በኢንተርኔ መረጃ መረብ ላይ የመድፈጣቸው ምልክት እየሆነ ነው፡፡  

 

በምእራቡ አለም በአማካይ በቀን ወስጥ ልጆች ለመገናኛ ብዙሃን የሚጋለጡበት አማካይ ሰአት በ1999 7፡29፣ በ2004 ወደ 8፡33 ሲያድግ፣ በ2009 ደግሞ ወደ 10፡45 አድጓል፡፡ይህ እንዲሆን ካስቻሉት ምክንያቶች አንዱ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ ከአንድ በላይ የሆኑ ነገሮችን ደራርበው ከመመልከታቸው የተነሳ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የ2004ቱን የ8፡33 ሰአት መልእክት ልጆች የፈፉት በ6፡30 ብቻ ነው፡፡ በአንጻሩ ግን ከወላጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጠቅላላ ጊዜ 2፡17 ደቂቃ አይበልጥም፡፡ ይህንን የተገነዘቡ በወጣቶች ባህሪ ዙሪያ ጥናት የሚያደርጉ ተመራማሪዎችም እድሜያቸው ከ8-18 ያሉትን ልጆች የመገናኛ ብዙሃን ትውልድ ብለው ሲጠሩዋቸው መደመጡ ከዚህ አይነቱ እውነታ የተነሳም በእርግጥም አይገርምም፡፡ ከዚህም የተነሳም ደግሞ ታዳጊ ወጣቶችን ለመረዳት የሚደረገው ማንኛውም ጥረት መገናኛ ብዙሃንና ተያይዞ የሚያመጣውን ተጽእኖ መመልከትን የግድ አድርጎታል ፡፡ 

 

ከመገናኛ ብዙሃን ውስጥ ደግሞ ፊልሞች በሀገራችን የሚጫወቱት ሚና ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ይህን ለመገንዘብ ደግሞ በየሰፈራችን ፊልሞችን በቀላል ዋጋ ልንከራያቸው የምንችልባቸውን መንገዶችንም እንካችሁ እነዚህ ታዳጊ ወጣቶች እንደሚባሉ ልብ ልንል ያስፈልገናል፡፡ ለነገሩ ፊልሞች እንደድሮ ተቀድተው ሳሎኖቻችን ባሉ ቴሌቪዢን መስኮቶች ወይም በየሰፈሩ ባሉ ቪዲዮ ቤቶች እና ጥቂት ሲኒማ ቤቶች ብቻ ሳይሆን የሚደመጡት በኮምፒውተሮች፣ በአይፓድ እንዲሁም በስልኮቻችን ስክሪኖች መሆኑ ለሁሉም ሰው ግልጥ ነው፡፡ ከነዚህ ጋር ተያይዞም ደግሞ ካለቤተሰብ ከለላ ታዳጊ ወጣቶች ያለማንም ቁጥጥር ፊልሞችን ብቻቸውን መኮምኮም የሚችሉበት አጋጣሚዎች ተፈጥረውላቸዋል፡፡ ታዳጊ ወጣቶች በነዚህ ፊልሞች ውስጥ ሃሳባቸውና አመለካከታቸው እየተመሰጠ በሄደ ቁጥርም፣ ቤተሰቦቻቸው ስሜቶቻቸውንና ፍላጎቶቻቸውን እንደማይረዱላቸውም ማሰባቸውና ድሮም ከባህላችን ተጽእኖ የተነሳ በልጆችና በቤተሰቦች መካከል ያለውን ትስስር በቋፍ ከነበረበትም፣ ወደ አለመግባባትና ወደ ጥል በአብዛኛው እያደላ መሄዱን መመልከት እንችላለን፡፡

 

ፊልም ለታዳጊ ወጣቶች ምንድን ነው? በልባቸውና በህይወታቸው ውስጥስ ምን ያህል ስፍራ አለው? መልሱ ፊልም ለነዚህ ታዳጊ ወጣቶች ሁሉንም ነገር ነው፡፡ ጓደኞቻቸው መካከል ተቀባይነት ያላቸውን ባህሪዎች የሚቀስሙበት ስፍራ፣ በህይወት የሚፈልጉዋቸውን ነገሮች የሚቀረጹበት ስፍራ፣ የማወቅ ጉጉታቸውን የሚሞላላቸው፣ በተለያያ ጊዜ  ለሚመጡባቸው ስሜቶቻቸው መፍቴህ የሚያገኙበት ቦታ ነው፡፡ አዎን ፊልም ለብዙ ታዳጊ ከተሜ ወጣቶች ታላቅ ጓደኛቸውና ወንድማቸው ነው፡፡ ይህን ለመመለከት ደግሞ ለረጅም ጊዜ ተለያይተው የቆዩና የተነፋፈቁ የልብ ወዳጆች ሲጨዋወቱ መመልከት በእርግጥም ጠቃሚ ነው፡፡ ምን አዲስ ነገር አለ ከሚለው ጥያቄ ጋርም ተታከው የሚመጡት የፊልሞች ርእሰጉዳይ እየሆኑ መምጣታቸው እሙን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚጠቁመን ነገር  ፊልሞች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የወጣቱ ማህበረሰብ ልማድ መገለጫ መሆናቸውን አመልካች ነው፡፡፡ ከዚህም የተነሳም ለአብዛኞቹ ከተሜ ወጣቶች ፊልሞች በእርግጥም ከጊዜ ወደ ጊዜ አብረዋቸው የሚኖሩ ደባል ወይም ተሸሽተው ማምለጥ የማይቻሉ ጎረቤቶቻቸው  እየሆኑ እንደመጡ ከማንም ልንደብቅ የማንችለው ሃቅ ነው ፡፡ 

 

ከተወሰኑ ጊዜያት ጀምሮ ደግሞ ወጣቶችን አላማ ተደርገው የሚሰሩ ፊልሞችም መጠናቸው እየበረከተ መጥቷል፡፡ ለምን ለሚለውም በርካታ መልሶች በመላመትነት ቢቀርቡም ሶሰቱ ግን ጉልህ ሆነው ይታያሉ፡፡ አንደኛው፡- ልጆች ለመዝናናት በፍጆታነት ሊያውሉት የሚችሉት ገንዘብ ስላላቸውና ይህንን ለመቀራመት ስለታሰበ የሚል ነው፡፡ እንደ ወላጅ መርሳት የማይገባን ነገር ፊልሞችን የሚያመርቱት ኩባንያዎች ልጆቻችንን በዋነኛነት የሚቀራመቱዋቸው ገበያዎቻቸው እንጂ በስስት የሚጠነቀቁላቸው ተንከባካቢ እረኞቻቸው አይደሉም፡፡ ኩባንያዎቹ ከምንደኞችም የከፉ ትርፍን ማግበስበስን በዋነኛነት ታሳቢ ያደረጉ ሰግብግብ ተቋማት ናቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ ቅኝታቸው ልጆቾ የሚያስፈልጋቸውን መመገብና ማጎልበት አለመሆኑ ሊዘነጋ አያስፈልግም፡፡ 

 

 ሁለተኛው፡- ዛሬ ላይ የምናያቸው ልጆች ለወደፊት በማደግ ሸማች ቤተሰቦች መሆናቸው አይቀርም የሚል ተስፋን በሰነቀ እይታ ገና ከአሁኑ ደንበኛ እንዲሆኑ ለመኮትኮት ያሰበ መሆኑንንም ጭምር ነው ፡፡ በሌላ አነጋገር ፊልሞቹ የልጆቾን የህይወት ጣእምና ምልከታ በመቃኘት ሂደት ውስጥ የሚጫወቱት ሚና አናሳ ተደርጎ የሚገመት መሆን የለበትም፡፡ ፊልሞች እንካችሁ በሚል ገና በጨቅላነት በጣፋጭ እየለወሱ የሚያቀርቡዋቸው ነገሮች ዝና፣ ንዋይ፣ እና በጋብቻ አጥር ያልታጠረ ወሲብ መሆናቸው ያደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ አንዳንድ ፊልሞች ከክርስቲያናዊ እሴት ጋር የማይገጥሙ ባህሪያትን አንቆለጳጵሶ በማሳየት በተቃርኖው ደግሞ ልንገዛላቸው የሚያስፈልጋቸውን መርሆች አኮስሶ በማቅረብ የተዋጣላቸው መሆናቸውን መገንዘብ ያሻል፡፡ ሶስተኛው፡- ፊልሙን የሚሰሩ ሰዎች ያጡትን የታዳጊነት ጊዜያት በማሰብ በውክልና ምኞቶቻቸውን የሚፈጽሙባቸው የእጅ ስራዎቻቸው መኆናቸውን መገንዘብም ይጠቅማል፡፡ ይህን ሲያደርጉም ለልጆቹ ሙከራ የሚሆኑ አሉታዊ ነገሮችንም እንካችሁ ጭምር ሊሉዋቸው እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

በ1960ዎቹ የተደሩገ ጥናቶች የሚያመለክቱት እድሜያቸው ከ13-19 ባሉ ልጆች ውስጥ ከፍተኛ ተጽእኖን እያደረሱ ያሉ ሃይላትና ተቋማት እነማን ናቸው የሚለውን ለማጥናት ሙከራ ተደርጎ ነበር፡፡ የጥናት ውጤቱም ባላቸው ተጽእኖ ቅደም ተከተል አራት ነገሮችን ነቅሶ ባላቸው ተጽእኖ ቅደም ተከተልም ደረጃም ጭምር አውጥቶም ነበር፡፡ በጊዜውም ቤተሰብ የመጀመሪያውን የክብር ደረጃ ይይዝ የነበረ ሲሆን፣ በሁለተኛነት ትምህርት ቤት ፣ በሶስተኛነት ጓደኞችና የእድሜ አቻዎች ሲሆኑ ፣ በአራተኛነት ደግሞ ቤተክርስቲያን ነበረች፡፡ በዚህ ዘመን ታዲያ ልጆች በዋነኛነት ያንጸባርቁት የነበረው ባህሪ፣ አስተሳሰብና ስሜት የቤተሰቦቻቸውን አይነት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከተለያዩ ምንጮች የሚሰሙዋቸው ነገሮች እምብዛም ስለማይለያዩ ወይም ስለማይቃረኑ ህይወትን የሚመለከቱበት መነጽርም ይህን ያህል የተምታታና ከትክክለኛው አቅጣጫም የሳተ አልነበረም፡፡ ነገር ግን በዚህ መልኩ ረጅም ጊዜ ነገር አልቀጠለም፡፡ 

 

ከሃያ አመት በኋላ ፣ ማለትም በ1980ዎች፣ የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት ደግሞ የቅድሚያውን ደረጃ ጓደኞችና የእድሜ አቻዎች የወሰዱት ሲሆኑ ቤተሰብ በሁለተኛነት እየለጠቀ ሲከተል፣ የመገናኛ ብዙሃን ሶስተኛ ሲሆኑ ፣ ትምህርት ቤት አራተኛ ደረጃን ሲይዝ ቤተክርስቲያን ከደረጃ ምድቡ ወርዷል፡፡ በኒዚህ ጊዜያት ደግሞ ልጆች በዋነኛነት ያሳዩት የነበረው መልክ ይመስል የነበረው የእድሜ አቻዎቻቸው የሆኑ ጓደኞቻቸውን ነበር፡፡ እናም ከመልካም ጓደኛ ጋር መዋል የቻሉት ባህሪያቸው በዛው መልኩ ሲቀየር ጥሩ ባህሪ ከሌላቸው ጋር የነበሩት ደግሞ እንደዚያው ባህሪያቸው ይበላሽ ነበር፡፡  እዚህ ጋር ልብ ማለት ያለብን ቤተክርስቲያን በእነዚህ ታዳጊ ልጆች ህይወት ውስጥ የምትጫወተው ሚናም እጅጉን እንደመነመነም ጭምር ነው፡፡ 

 

በቅርብ ጊዜ ይህ ጥናት ቢደገም ብለው ብዙዎች ሲተነብዩ የሚሉት መገናኛ ብዙሃን የቅድሚያውን ስፍራ እንደሚይዙና፣ የእድሜ አቻዎችና ጓደኞች ሁለተኛ ሲሆኑ፣ ቤተሰብ ሶስተኛ እና ትምህርት ቤት ደግሞ አራተኛ መሆኑ አይቀሩም፡፡ ይህ የሚጠቁመን ነገር የመገናኛ ብዙሃን ሚና በታዳጊ ወጣቶች ላይ እጅጉን ከፍተኛ መሆኑና እነዚህን ልጆች ለመረዳት የሚደረገውም ጥረት በምንም መልኩ ችላ ሊባል እንደማያስፈልግም ነው፡፡ ከመገናኛ ብዙሃን ለጥቀው የሚመጡትም የእድሜ አቻዎቻቸው መሆናቸውና እነርሱም ራሳቸው በተመሳሳይ ተጽእኖ ውስጥ ያሉ ስለሆኑ ከመገናኛ ብዙሃን የሰሙዋቸውንና መከተል የማያስፈልጋቸውን አንዳድ ባህሪያት፣ ስሜቶችና እንዲሁም አስተሳሰቦች መፈተሽ የሚችለሁባቸው እድል ካለመኖሩ የተነሳ በነገሩ ተጠቂነታቸው እጅጉን እየጨመረ መምጣቱ አይቀርም፡፡ እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ደግሞ በእርግጥም የሚያሳስብ ነው፡፡ ጆሹዋ ሜይሮዊትዝ ቴሌቩዥን በልጆች ላይ እያደረሰ ያለው ነገር ሲገልጽ፣ ልጆች መንገድ ለማቋረጥ እንኳ ገና ፍቃድ ሳይሰጣቸው አለምን እንዲጓዙት ያደርጋቸዋል  በማለት አደጋውን ገልጾታል፡፡

 

  1. መልእክቴ

መጽሐፍ ቅዱሳዊው ምክር ደግሞ ፣ “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፥ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም።”  (ምሳ 22፡6) የሚል ነው፡፡ይህ ክፍል ፣ወላጆች ልጆችን በማሳደግ ሂደት ውስጥ ከአምላክ የተቀበሉት ሃላፊነትና አደራ መኖሩንና በጽኑእ ያሳስበናል፡፡ የሚጫወቱትም ንቁ ተሳትፎ ልጆች ወደ ጉልምስና በሚመጡበት ጊዜ የሚኖራቸውን ማንነት ቅርጽ በማሲያዝ ሂደት ውስጥ እጅጉን ወሳኝ መሆኑን ያመላክታል፡፡ የወላጅ ድርሻም በዋነኛነት መንገድ አመላካችና መሪ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ያደረግነው ምሪት ልጁ ማደግ ብቻ አይደለም፣ በሚሸመግልበት ጊዜ ሁሉ አሻራው በመታየት እንደሚቀጥልም አመልካች ነው፡፡ እንዲሁም በሌላ ስፍራ መጽሐፍ ቅዱሳችን ሲናገር ጻድቅ ያለ ነውር ይሄዳል ልጆቹም ከእርሱ በኋላ ምስጉኖች ናቸው በማለት የእኛ አካሄድ በልጆቻችን ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ያስረዳናል (ምሳ 20፡7)፡፡ አፍሪካውያኑ ኒያንጃዎችም ይህንን በምሳሌ ሲገልጹት ፣ “ሁል ጊዜ የሚደነስበት ቦታ ያደገ ልጅ መደነስ አያቅተውም፡፡” ይሉናል፡፡ ይህ ክፍል ደግሞ አጽኖት በመስጠት የሚናገረው ለልጆች የምናደርገው ምሪትና እገዛ በቃላታችን ጋጋታዎች ውስጥ ብቻ የሚገለጥ ሳይሆን በአኗኗር ቅኝታችን ውስጥም የሚታይ መሆኑንና ልጆቻችንም እንደተምሳሌት እኛን በመቁጠር እንደሚሄዱበትም ጭምር ነው፡፡ የዛሬው መልእክቴ አጭርና ግልጽ ነው፡፡ ለልጆቻችን ወላጆቻቸው እንሁን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚመለከቱትን እና የሚሰሙትን የመገናኛ ብዙሃን በመምረጥ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ በመሆን መልካቸውን ለመቅረጽ የተሰጠንን ሀላፊነት እንወጣ የሚል ጥሪ ነው፡፡ በልጆቻችን ህይወት ውስጥ ባህሪን በመቅረጽ ሂደት በማሳተፍ ወላጅነታችን እናረጋግጥ የሚል ጥሪ ነው፡፡ በሚቀጥለው ጽሑፌ ተጨማሪ ነገሮችን ስለፊልም ለመነጋገር ቃል እየገባው ለዛሬው ግን እዚህ ጋር ልሰናበት፡፡ በማክበር አይኖቻችሁን ስለሰጣችሁኝ ቸር ያሰነብትልኝ፡፡

 

 

1Rose M. Kundanis፣ Children, Teens, Families, and Mass Media: The Millennial Generation, (Mahwah: Lawrence Erlbaum Associates, 2008),122

2 Salman Akhtar፣The electrified mind: development, psychopathology, and treatment in the era of cell phones and the internet፣(Lanham, Md. : Jason Aronson, 2011.)፣22

3 Milton Chen፣Education Nation: Six Leading Edges of Innovation in our Schools፣(San Francisco, Calif. : Jossey-Bass, 2010) 142

4 Stanley J Baran; Dennis K Davis፣Mass communication theory : foundations, ferment, and future፣(Boston, MA : Wadsworth Cengage Learning, 2009)፣193

5 Ibid

 

Read 53085 times Last modified on Saturday, 12 July 2014 10:29
Tekalign Nega

Tekalign Nega is a columnist of Hinstet, Psychology corner. He is a lecture at Addis Ababa University. He specialized at post graduate level Accounting and Finance, counseling psychology, and theology. He teaches also at theological colleges, trains leaders, and preaches the word of God upon invitation. He has burden to the church of Christ in various areas of counseling and Islam. Currently he is a PhD student at Tilburg University, the Netherlands.

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Most Read

ከእግዚአብሔር ጋር የሚሠራ...

Written bySolomon Abebe Gebremedhin

It is Okay not t...

Written byMeskerem T. Kifetew, PharmD

Lust On a Driver...

Written byMeskerem T. Kifetew, PharmD

የአገር ያለህ!...

Written byNegussie Bulcha

 

 

 

.

Right Now

We have 110 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.